የማቴዎስ ወንጌል 26:20-29
የማቴዎስ ወንጌል 26:20-29 መቅካእኤ
በመሸም ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀመዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ። ሲበሉም ሳሉ “እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አለ። እጅግም አዝነው እያንዳንዳቸው “ጌታ ሆይ! እኔ እሆንን?” ይሉት ጀመር። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ከእኔ ጋር እጁን በሳሕኑ ውስጥ የሚያጠልቀው፥ እርሱ አሳልፎ ይሰጠኛል። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰውን ልጅ አልፎ ለሚሰጥ ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር።” አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም መልሶ “መምህር ሆይ! እኔ እሆንን?” አለ፤ “አንተ አልህ” አለው። ሲበሉም ሳሉ ኢየሱስ ኅብስትን አንሥቶ ባረከ፤ ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና “እንካችሁ፥ ብሉ፤ ይህ ሥጋዬ ነው” አለ። ጽዋውንም አንሥቶ አመስግኖ ሰጣቸው፤ እንዲህ ብሎ ሰጣቸው “ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የኪዳን ደሜ ይህ ነው። በአባቴ መንግሥት አዲሱን ከእናንተ ጋር እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ከዛሬ ጀምሬ ከዚህ ወይን አልጠጣም እላችኋለሁ።”


