ኢየሱስ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ሲሄድ ደቀመዛሙርቱ የቤተ መቅደሱን ግንቦች ሊያሳዩት ወደ እርሱ ቀረቡ። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ የሚቀር የለም።” በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀመዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው “እስቲ ንገረን፤ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድነው?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። ብዙዎች ‘መሢሑ እኔ ነኝ’ እያሉ በስሜ ይመጣሉና ብዙዎችንም ያስታሉ። ጦርነትንና የጦርነትን ወሬ ትሰማላችሁ፤ አስተውሉ፥ አትደንግጡ፥ ይህ ሊሆን ግድ ነውና፤ ነገር ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፤ ራብና የምድር መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፤ እነዚህ ሁሉ የምጥ መጀመሪያ ናቸው። “በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ይገድሉአችኋልም፤ ስለ ስሜም በሕዝቦች ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። በዚያን ጊዜ ብዙዎች ይሰናከላሉ፤ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ፤ እርስ በርሳቸውም ይጠላላሉ፤ ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ፤ ከሕገ ወጥነት ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች። እስከ መጨረሻው የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። ለሕዝቦች ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥቱ ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ በዚያን ጊዜ መጨረሻው ይመጣል። “ስለዚህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኩሰት በተቀደሰው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፤ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራሮች ይሽሹ፤ በጣራ ላይ ያለ በቤቱ ያለውን ሊወስድ አይውረድ፤ በእርሻም ያለ ልብሱን ሊወስድ ወደ ኋላው አይመለስ። በነዚያ ቀናት ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው። ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ፤ በዚያን ጊዜ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ ከእንግዲህ ወዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና። እነዚያ ቀኖች ባያጥሩ ኖሮ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነ ነበር፤ ነገር ግን ስለ ተመረጡት ሰዎች እነዚያ ቀኖች ያጥራሉ።
የማቴዎስ ወንጌል 24 ያንብቡ
ያዳምጡ የማቴዎስ ወንጌል 24
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 24:1-22
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች