የማቴዎስ ወንጌል 2:1-9

የማቴዎስ ወንጌል 2:1-9 መቅካእኤ

ኢየሱስም በይሁዳ ቤተልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰብአ ሰገል ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፥ እንዲህም አሉ፦ “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና።” ንጉሡ ሄሮድስ ሰምቶ ታወከ፤ መላዋ ኢየሩሳሌምም ከእርሱ ጋር ታወከች፤ ሊቃነ ካህናትንና የሕዝቡን ጻፎች ሁሉ ሰብስቦ ክርስቶስ የት እንደሚወለድ ጠየቃቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት፦ በይሁዳ ቤተልሔም ነው፤ በነቢዩ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና፤ “በይሁዳ ምድር የምትገኚ አንቺ ቤተልሔም፥ ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሽም፤ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ መሪ ከአንቺ ይወጣልና።” ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገልን በስውር ጠርቶ ኮከቡ የታየበትን ዘመን ከእነርሱ ተረዳ። እንዲህ ብሎም ወደ ቤተልሔም ላካቸው፦ “ሂዱ፤ ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔ ደግሞ መጥቼ እንድሰግድለት ንገሩኝ” አላቸው። እነርሱም ንጉሡን ከሰሙ በኋላ ሄዱ፤ እነሆ፥ በምሥራቅ ያዩት ኮከብ ሕፃኑ ባለበት ላይ መጥቶ እስኪቆም ድረስ ይመራቸው ነበር።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች