የማቴዎስ ወንጌል 15:21-31

የማቴዎስ ወንጌል 15:21-31 መቅካእኤ

ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና አገር ሄደ። እነሆ አንዲት ከነዓናዊት ሴት ከዚያ አገር መጥታ “የዳዊት ልጅ ጌታ ሆይ ማረኝ፤ ሴት ልጄ በጋኔን ክፉኛ ተይዛለች” እያለች ጮኸች። እርሱ ግን አንድ ቃልም አልመለሰላትም። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው “ከኋላችን እየጮኸች ነውና አሰናብታት” እያሉ ለመኑት። እርሱም “የተላክሁት ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች ነው እንጂ ለሌላ አይደለም” ሲል መለሰ። እርሷ ግን መጥታ እየሰገደች “ጌታ ሆይ! እርዳኝ” አለች። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላት “የልጆችን እንጀራ ወስዶ ለቡችሎች መጣል መልካም አይደለም።” እርሷም “አዎን ጌታ ሆይ! ነገር ግን ቡችሎችም ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ” አለች። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ “አንቺ ሴት፥ እምነትሽ ታላቅ ነው፤ እንደ ፍላጎትሽ ይሁንልሽ” ሲል መለሰላት። ሴት ልጇም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ተፈወሰች። ኢየሱስ ከዚያ አልፎ ወደ ገሊላ ባሕር አጠገብ መጣ፤ ወደ ተራራም ወጥቶ እዚያ ተቀመጠ። ብዙ ሕዝብም አንካሶችን፥ ዕውሮችን፥ ሽባዎችን፥ ዲዳዎችን፥ ሌሎችንም ብዙ ይዘው ወደ እርሱ መጡ፥ በኢየሱስም እግር ሥር አስቀመጡአቸው፤ እርሱም ፈወሳቸው። ሕዝቡም ዲዳዎች ሲናገሩ፥ ሽባዎች ሲፈወሱ፥ አንካሶች ሲራመዱ፥ ዕውሮችም ሲያዩ አይተው ተደነቁ፤ የእስራኤልንም አምላክ አከበሩ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች