የማቴዎስ ወንጌል 13:24-52

የማቴዎስ ወንጌል 13:24-52 መቅካእኤ

ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው፤ እንዲህም አለ “መንግሥተ ሰማያት በእርሻው ላይ መልካም ዘርን የዘራ ሰውን ትመስላለች። ሰዎቹ ተኝተው ሳለ፥ ጠላት መጥቶ በስንዴው መካከል እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ። ስንዴው በቅሎ ባፈራ ጊዜ እንክርዳዱም ያንጊዜ ታየ። የባለቤቱ ባርያዎችም ቀርበው ‘ጌታ ሆይ! በእርሻህ ላይ መልካም ዘር ዘርተህ አልነበረምን? ታዲያ እንክርዳዱ ከየት መጣ?’ አሉት። እርሱም ‘ጠላት ይህን አደረገ’ አላቸው። ባርያዎቹም ታዲያ ሄደን እንድንነቅለው ትፈልጋለህን?” አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው እንክርዳዱን ስትሰበስቡ ስንዴውን ከእርሱ ጋር እንዳትነቅሉት አይሆንም። እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ ተዉአቸው፤ በመከር ጊዜ አጫጆቹን “አስቀድማችሁ እንክርዳዱን በእሳትም ለማቃጠል ሰብስባችሁ በየነዶው እሰሩት፤ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ክተቱት፤ እላቸዋለሁ።” ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው፤ እንዲህም ሲል ነገራቸው “መንግሥተ ሰማያት አንድ ሰው ወስዶ በእርሻው የዘራትን የሰናፍጭ ዘር ትመስላለች፤ እርሷ ከዘሮች ሁሉ ያነሰች ናት፤ በአደገች ጊዜ ግን፥ ከአትክልቶች ትበልጣለች የሰማይም ወፎች መጥተው በቅርንጫፎችዋ እስኪሰፍሩ ድረስ ዛፍ ትሆናለች።” ሌላ ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማያት አንዲት ሴት ወስዳ ሁሉ እስኪቦካ ድረስ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት ውስጥ የሸሸገችውን እርሾ ትመስላለች።” ኢየሱስም ለሕዝቡ ይህን ሁሉ በምሳሌ ነገራቸው፤ ያለ ምሳሌም ምንም አልነገራቸውም። ይህም በነቢዩ እንዲህ ተብሎ የተነገረው እንዲፈጸም ነው፤ “አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውንም እናገራለሁ፤” በዚያን ጊዜ ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ገባ። ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው “የእርሻውን እንክርዳድ ምሳሌ ትርጒም ንገረን፤” አሉት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “መልካሙን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ እርሻውም ዓለም ነው፤ መልካሙ ዘር የመንግሥቱ ልጆች ናቸው፤ እንክርዳዱ ደግሞ የክፉው ልጆች ናቸው፤ የዘራው ጠላት ደግሞ ዲያብሎስ ነው፤ መከሩም የዓለም መጨረሻ ነው፤ አጫጆቹ መላእክት ናቸው። እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል ሁሉ በዓለም መጨረሻም እንዲሁ ይሆናል። የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፤ ከመንግሥቱም እንቅፋቶችን ሁሉና ዓመፃን ይሰበስባሉ፤ ወደ እቶን እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ያበራሉ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ። “መንግሥተ ሰማያት አንድ ሰው በእርሻ ውስጥ አግኝቶ መልሶ የሸሸገው የተሰወረ መዝገብ ትመስላለች፤ ከደስታውም ብዛት ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጦ ያንን እርሻ ገዛው። “ደግሞ መንግሥተ ሰማያት ክቡር ዕንቁ የሚፈልግ ነጋዴን ትመስላለች፤ ዋጋዋ እጅግ ውድ የሆነ አንዲት ዕንቁ ባገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ገዛት። “ደግሞም መንግሥተ ሰማያት ወደ ባሕር የተጣለችና ከሁሉም ዓይነት ዓሣ የሰበሰበች መረብን ትመስላለች፤ በሞላች ጊዜ ወደ ወደቡ አወጡአት፤ ተቀምጠውም መልካሞቹን ለቅመው በዕቃዎች ውስጥ አስቀመጡ፤ ክፉውን ግን ጣሉት። በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል፤ መላእክት መጥተው ክፉዎችን ከጻድቃን ይለዩአቸዋል፤ ወደ እቶን እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያም ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።” “ይህን ሁሉ አስተዋላችሁን?” አላቸው፤ “አዎን” አሉት። እርሱም “ስለዚህ የመንግሥተ ሰማያት ደቀመዝሙር የሆነ ጸሐፊ ሁሉ ከመዝገቡ አዲሱንና አሮጌውን የሚያወጣ ባለቤትን ይመስላል፤” አላቸው።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች