የማቴዎስ ወንጌል 13:18-34

የማቴዎስ ወንጌል 13:18-34 መቅካእኤ

እንግዲህ እናንተ የዘሪውን ምሳሌ ስሙ። የመንግሥቱን ቃል ሰምቶ የማያስተውል ሁሉ፥ ክፉው መጥቶ በልቡ የተዘራውን ይነጥቀዋል፤ በመንገድ ዳር የተዘራው ይህ ነው። በጭንጫማ መሬት ላይ የተዘራው ደግሞ ይህ ቃሉን ሰምቶ ወዲያው በደስታ የሚቀበለው ነው፤ በራሱ ሥር የለውም፤ ነገር ግን ለትንሽ ጊዜ ይቆያል፥ በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በመጣ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላል። በእሾህ መካከል የተዘራው፥ ይህ ቃሉን የሚሰማ ነው፤ ነገር ግን የዚህ ዓለም ጭንቀትና የሃብት ማታለል ቃሉን ያንቃል፤ የማያፈራም ይሆናል። በመልካም መሬት የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ነው፤ እርሱም ፍሬ ያፈራል፤ አንዱ መቶ፥ አንዱ ስድሳ አንዱም ሠላሳ ይሰጣል። ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው፤ እንዲህም አለ “መንግሥተ ሰማያት በእርሻው ላይ መልካም ዘርን የዘራ ሰውን ትመስላለች። ሰዎቹ ተኝተው ሳለ፥ ጠላት መጥቶ በስንዴው መካከል እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ። ስንዴው በቅሎ ባፈራ ጊዜ እንክርዳዱም ያንጊዜ ታየ። የባለቤቱ ባርያዎችም ቀርበው ‘ጌታ ሆይ! በእርሻህ ላይ መልካም ዘር ዘርተህ አልነበረምን? ታዲያ እንክርዳዱ ከየት መጣ?’ አሉት። እርሱም ‘ጠላት ይህን አደረገ’ አላቸው። ባርያዎቹም ታዲያ ሄደን እንድንነቅለው ትፈልጋለህን?” አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው እንክርዳዱን ስትሰበስቡ ስንዴውን ከእርሱ ጋር እንዳትነቅሉት አይሆንም። እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ ተዉአቸው፤ በመከር ጊዜ አጫጆቹን “አስቀድማችሁ እንክርዳዱን በእሳትም ለማቃጠል ሰብስባችሁ በየነዶው እሰሩት፤ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ክተቱት፤ እላቸዋለሁ።” ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው፤ እንዲህም ሲል ነገራቸው “መንግሥተ ሰማያት አንድ ሰው ወስዶ በእርሻው የዘራትን የሰናፍጭ ዘር ትመስላለች፤ እርሷ ከዘሮች ሁሉ ያነሰች ናት፤ በአደገች ጊዜ ግን፥ ከአትክልቶች ትበልጣለች የሰማይም ወፎች መጥተው በቅርንጫፎችዋ እስኪሰፍሩ ድረስ ዛፍ ትሆናለች።” ሌላ ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማያት አንዲት ሴት ወስዳ ሁሉ እስኪቦካ ድረስ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት ውስጥ የሸሸገችውን እርሾ ትመስላለች።” ኢየሱስም ለሕዝቡ ይህን ሁሉ በምሳሌ ነገራቸው፤ ያለ ምሳሌም ምንም አልነገራቸውም።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች