የሉቃስ ወንጌል 8:9-17

የሉቃስ ወንጌል 8:9-17 መቅካእኤ

ደቀ መዛሙርቱም፦ “ይህ ምሳሌ ትርጓሜው ምንድነው?” ብለው ጠየቁት። እርሱም “ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለሌሎች ግን እያዩ እንዳያዩ እየሰሙም እንዳያስተውሉ በምሳሌዎች ይነገራቸዋል” አላቸው። “የምሳሌውም ትርጒም ይህ ነው፦ ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው። በመንገድ ዳርም ያሉት የሰሙት ናቸው፤ ከዚያ በኋላም አምነው እንዳይድኑ ዲያብሎስ መጥቶ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል። እንዲሁም በዐለት ላይ ያሉት ቃሉን በሰሙ ጊዜ በደስታ የሚቀበሉት ናቸው፤ ነገር ግን ሥር የላቸውም፥ እነርሱም ለጊዜው ብቻ ያምናሉ እንጂ በፈተና ጊዜ ይክዳሉ። በእሾህም መካከል የወደቁት እንዲሁ ከእነዚያ ከሰሙት ወገን ናቸው፤ በመንገዳቸውም በዚህ የምድራዊ ሕይወት ምኞትና ሀብት እንዲሁም ምቾት ይታነቃሉ፤ ሙሉ ፍሬም አያፈሩም። በመልካም መሬት ላይ ያሉት ደግሞ ቃሉን በመልካምና በቅን ልብ ሰምተው የሚጠብቁ፥ በመጽናትም ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው። “መብራትንም አብርቶ በእንቅብ የሚከድነው ወይም ከአልጋ በታች የሚያኖረው ማንም የለም፤ ይልቅስ የሚገቡት ሰዎች ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያኖረዋል። የማይገለጥ ምንም የተሰወረ የማይታወቅም ወደ ብርሃንም የማይመጣ ምንም የተሸሸገ ነገር የለምና።