የሉቃስ ወንጌል 20:9-18

የሉቃስ ወንጌል 20:9-18 መቅካእኤ

ይህንንም ምሳሌ ለሕዝቡ ይነግራቸው ጀመር። “አንድ ሰው የወይን አትክልት ተከለ፤ ለወይን ጠባቂዎች አከራይቶ ለረጅም ጊዜ ወደ ሌላ አገር ሄደ። ጊዜውም ሲደርስ ከወይኑ አትክልት ፍሬ እንዲሰጡት አንድ አገልጋይ ወደ ተከራዮቹ ላከ፤ ጠባቂዎቹ ግን ደበደቡትና ባዶ እጁን ሰደዱት። እንዲሁም ሌላ አገልጋይ ላከ፤ እነርሱም ያን ደግሞ ደበደቡት፥ አዋርደውም ባዶውን ሰደዱት። እንደገናም ሦስተኛውን ላከ፤ እነርሱም ይኸኛውን ደግሞ አቁሰለው አስወጡት። የወይኑ አትክልት ጌታም ‘ምን ላድርግ? የምወደውን ልጄን እልካለሁ፤ ምናልባት እርሱን አይተው ያፍሩታል፤’ አለ። ተከራዮቹ ግን አይተውት እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ ‘ወራሹ ይህ ነው፤ ርስቱ ለእኛ እንዲሆን ኑ እንግደለው፤’ አሉ። ከወይኑም አትክልት ወደ ውጭ አውጥተው ገደሉት። እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ ምን ያደርጋቸዋል? ይመጣል እነዚህንም ተከራዮች ያጠፋል፥ የወይኑንም አትክልት ለሌሎች ይሰጣል።” ይህንንም በሰሙ ጊዜ “ይህስ በጭራሽ አይሁን፤” አሉ። እርሱ ግን ወደ እነርሱ ተመልክቶ “እንግዲህ ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፥ እርሱ ነው የማዕዘን ራስ የሆነው፤’ ተብሎ የተጻፈው ምን ማለት ነው? በዚያም ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ሁሉ ይሰባበራል፤ የሚወድቅበትን ሁሉ ግን ይጨፈልቀዋል፤” አለ።