የሉቃስ ወንጌል 15:17-32

የሉቃስ ወንጌል 15:17-32 መቅካእኤ

ወደ ልቡም ተመልሶ እንዲህ አለ ‘ምግብ የሚተርፋቸው የአባቴ ተቀጣሪዎች ስንት ናቸው? እኔ ግን ከዚህ በራብ እጠፋለሁ። ተነሥቼም ወደ አባቴ እሄዳለሁና “አባቴ ሆይ! በሰማይና በፊትህ በደልሁ፤ ወደፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከተቀጣሪዎችህ እንደ አንዱ አድርገኝ፤”’ እለዋለሁ። ተነሥቶም ወደ አባቱ መጣ። እርሱም ገና ሩቅ ሳለ አባቱ አየውና አዘነለት፤ ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው። ልጁም ‘አባቴ ሆይ! በሰማይና በፊትህ በደልሁ፤ ወደፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤’ አለው። አባቱ ግን አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው ‘ፈጥናችሁ ከሁሉ የተሻለ ልብስ አምጡና አልብሱት፤ በጣቱ ቀለበት በእግሩም ጫማ አጥልቁለት፤ የሰባውን ፍሪዳ አምጥታችሁ እረዱት፤ እንብላም ደስም ይበለን፤ ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና ደግሞም ሕያው ሆኖአል፤ ጠፍቶም ነበር ተገኝቶአልም።’ ደስ ይላቸውም ጀመር። “ታላቁ ልጁ በእርሻ ነበረ፤ መጥቶም ወደ ቤት በቀረበ ጊዜ የሙዚቃና የውዝዋዜ ድምፅ ሰማ፤ ከአገልጋዮቹም አንዱን ጠርቶ ‘ይህ ምንድነው?’ ብሎ ጠየቀ። እርሱም ‘ወንድምህ መጥቷል፤ በደኅና ስላገኘውም አባትህ የሰባውን ፍሪዳ አረደለት፤’ አለው። እርሱም ተቈጣ፤ ሊገባም አልፈለገም፤ አባቱም ወጥቶ ለመነው። እርሱ ግን መልሶ አባቱን ‘እነሆ፥ ይህን ያህል ዓመት አገለገልኩህ፤ ከትእዛዝህም ከቶ አልተላለፍሁም፤ ከወዳጆቼ ጋር እንድደሰት ለእኔ አንድ ጥቦት እንኳን ሰጥተኸኝ አታውቅም፤ ነገር ግን ይህ ልጅህ ገንዘብህን ከአመንዝራ ሴቶች ጋር አባክኖ በመጣ ጊዜ፥ የሰባውን ፍሪዳ አረድህለት፤’ አለው። እርሱ ግን እንዲህ አለው፦ ‘ልጄ ሆይ! አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፤ ለእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው፤ ዳሩ ግን ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበረ፤ ሕያው ስለ ሆነ ጠፍቶም ነበር፤ ስለ ተገኘ ደስ እንዲለን ፍሥሐም እንድናደርግ ይገባናል’።”