የሉቃስ ወንጌል 1:8-23
የሉቃስ ወንጌል 1:8-23 መቅካእኤ
እርሱም በክፍሉ ተራ በእግዚአብሔር ፊት በክህነት ሲያገለግል፥ እንደ ካህናት ሥርዓት ወደ ጌታ ቤተ መቅደስ ገብቶ ለማጠን ዕጣ ደረሰው። በዕጣንም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ በውጭ ቆመው ይጸልዩ ነበር። የጌታም መልአክ በዕጣኑ መሠዊያ ቀኝ ቆሞ ታየው። ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፤ በፍርሃትም ተዋጠ። መልአኩ ግን እንዲህ አለው፦ “ዘካርያስ ሆይ! ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ብለህ ትጠራዋለህ። ደስታና ሐሤትም ይሆንልሃል፤ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል። በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና፥ የወይን ጠጅም ሆነ የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ ገናም በእናቱ ማኅፀን ሳለ በመንፈስ ቅዱስ ይሞላል፤ ከእስራኤልም ልጆች ብዙዎችን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳል። እርሱም የተዘጋጀን ሕዝብ ለጌታ አሰናድቶ፥ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፥ የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ለመመለስ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል።” ዘካርያስም መልአኩን፦ “እኔ ሽማግሌ ነኝ፤ ሚስቴም በዕድሜዋ ገፍታለችና ይህንን በምን አውቃለሁ?” አለው። መልአኩም መልሶ፦ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ እንድነግርህም ይህችንም የምሥራች እንዳበሥርህ ተልኬአለሁ፤ እነሆም፥ በጊዜያቸው የሚፈጸሙትን ቃሎቼን ስላላመንህ፥ ይህ ነገር እስከሚሆንበት ቀን ድረስ አንደበትህ ይታሰራል፤ መናገርም አትችልም፤” አለው። ሕዝቡም ዘካርያስን ይጠብቁት ነበር፤ በቤተ መቅደስ ውስጥ በመዘግየቱም ተገረሙ። በወጣም ጊዜ ሊያናግራቸው አልቻለም፤ በቤተ መቅደስም ውስጥ ራእይ እንዳየ ተገነዘቡ፤ እርሱም በምልክት ያናግራቸው ነበር፤ ዲዳም ሆኖ ቆየ። የአገልግሎቱም ጊዜ እንደ ተፈጸመ ወደ ቤቱ ሄደ።



