ኦሪት ዘሌዋውያን 14
14
በሥጋ ደዌ የተጠቃውን ሰውና ቤቱን የማንጻት ሥርዓት
1ጌታም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ 2#2ነገ. 5፥10፤ 14፤ ማቴ. 8፥4፤ 10፥8፤ ማር. 1፥44፤ ሉቃ. 4፥27፤ 5፥14።“በመንጻቱ ቀን የለምጽ ደዌ ያለበት ሰው ሕግ ይህ ይሆናል፤ ወደ ካህኑ ይወስዱታል።#ዘሌ. 14፥48-53። 3#ዘሌ. 13፥46።ካህኑም ከሰፈር ወደ ውጭ ይወጣል፤ ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ የለምጹ ደዌ ለምጽ ካለበት ሰው ላይ ቢጠፋ፥ 4#ዘኍ. 19፥6።ካህኑ ስለሚነጻው ሰው በሕይወት ያሉ ሁለት ንጹሐን ወፎች፥ የዝግባም እንጨት፥ ቀይ ግምጃም፥ ሂሶጵም እንዲመጣለት ያዝዛል። 5ካህኑም ከሁለቱ ወፎች አንዱን በሸክላ ዕቃ ውስጥ በምንጭ ውኃ ላይ እንዲታረድ ያዝዛል። 6በሕይወት ያለውን ወፍ፥ የዝግባውንም እንጨት፥ ቀዩንም ግምጃ፥ ሂሶጱንም ወስዶ ይነክራቸዋል፥ በሕይወትም ያለውን ወፍ በምንጭ ውኃ ላይ በታረደው የወፍ ደም ውስጥ ይዘፍቀዋል። 7#ዘሌ. 16፥21-22።ከለምጽ ደዌ በሚነጻው ሰው ላይ ሰባት ጊዜ ይረጨዋል፤ ከዚያም ንጹሕ ነህ ይለዋል፥ በሕይወትም ያለውን ወፍ በተንጣለለው ሜዳ ላይ እንዲበር ይለቀዋል። 8#ዘሌ. 15፥13።የነጻውም ሰው ልብሱን ያጥባል፥ ጠጉሩንም ሁሉ ይላጫል፥ በውኃም ይታጠባል፥ ንጹሕም ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈር ይገባል፥ ነገር ግን ከድንኳኑ በውጭ ሆኖ ሰባት ቀን ይቀመጣል። 9በሰባተኛውም ቀን ጠጉሩን ሁሉ ይላጫል፤ ራሱንም፥ ጢሙንም፥ ቅንድቡንም፥ የገላውንም ጠጉር ሁሉ ይላጫል፤ ከዚያም ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፤ እርሱም ንጹሕ ይሆናል።
10“በስምንተኛውም ቀን ነውር የሌለባቸውን ሁለት ተባት ጠቦት፥ ነውር የሌለባትንም አንዲት የዓመት እንስት ጠቦት፥ ለእህሉም ቁርባን ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሦስት እጅ የሆነ በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ዘይትም ያለበትን አንድ የሎግ መስፈሪያ ይወስዳል። 11የሚያነጻውም ካህን የሚነጻውን ሰውና እነዚህን ነገሮች በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አጠገብ በጌታ ፊት ያኖራቸዋል። 12#ዘሌ. 7፥1-10።ካህኑም አንዱን ተባት ጠቦት ይወስዳል፤ እርሱንም ስለ በደል መሥዋዕት ያቀርበዋል፥ ጎን ለጎንም ዘይቱ ያለበትን የሎግ መስፈሪያውን፤ እነርሱንም ስለ መወዝወዝ ቁርባን በጌታ ፊት ይወዘውዛቸዋል።#ዘሌ. 7፥30። 13የኃጢአትን መሥዋዕትና የሚቃጠለውን መሥዋዕት በሚያርድበት በተቀደሰው ስፍራ ጠቦቱን ያርደዋል፤ እንደ ኃጢአት መሥዋዕቱም እንዲሁ የበደል መሥዋዕቱ ለካህኑ ይሆናል፤ እርሱም እጅግ የተቀደሰ ነው። 14#ዘሌ. 8፥23-24።ካህኑም ከበደል መሥዋዕት ደም ይወስዳል፤ እርሱም የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት ያስነካዋል። 15ካህኑም ከሎግ መስፈሪያው ውስጥ ያለውን ዘይት ወስዶ በግራ እጁ መዳፍ ላይ ያፈስሰዋል። 16ካህኑም በግራ እጁ መዳፍ ላይ ያለውን ዘይት በቀኝ ጣቱ ነክሮ ከዘይቱ በጌታ ፊት ሰባት ጊዜ በጣቱ ይረጫል። 17ካህኑም በእጁ መዳፍ ላይ ከተረፈው ዘይት የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት፥ የበደልም መሥዋዕት በሆነው ደም ላይ ያስነካዋል። 18#ዘሌ. 8፥12።ካህኑም በእጁ መዳፍ ላይ የተረፈውን ዘይት በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያደርግበታል፤ ከዚያም ካህኑ በጌታ ፊት ያስተሰርይለታል። 19#ዘሌ. 4።ካህኑም የኃጢአቱን መሥዋዕት ያቀርባል፥ ከርኩሰቱም ለሚነጻው ሰው ያስተሰርይለታል፤ ከዚያም በኋላ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያርዳል። 20#ዘሌ. 1።ካህኑም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቁርባን በመሠዊያው ላይ ያቀርባል፤ እንዲህም አድርጎ ካህኑ ያስተሰርይለታል፤ እርሱም ንጹሕ ይሆናል።
21 #
ዘሌ. 5፥7፤ 11፤ 12፥8። “ነገር ግን ድሀ ቢሆን ይህንንም ለማቅረብ በቂ ገንዘብ ባይኖረው፥ እንዲያስተሰርይለት ለበደል መሥዋዕት እንዲወዘወዝ አንድ ጠቦት፥ ለእህልም ቁርባን ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ አንድ እጅ የሆነ በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ አንድ የሎግ መስፈሪያም ዘይት ይወስዳል። 22ለመግዛትም አቅሙ የሚፈቅድለትን ያህል ሁለት ዋኖሶች ወይም የርግብ ግልገሎች፥ አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሌላውን ለሚቃጠል መሥዋዕት ያደርገዋል። 23በስምንተኛውም ቀን ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በጌታ ፊት ስለ መንጻቱ እንዲሆኑ ወደ ካህኑ ያመጣቸዋል። 24ካህኑም የበደሉን መሥዋዕት ጠቦትና ዘይትም ያለበትን የሎግ መስፈሪያ ይወስዳል፤ ካህኑም ለመወዝወዝ ቁርባን በጌታ ፊት ይወዘውዛቸዋል። 25የበደሉንም መሥዋዕት ጠቦት ያርዳል፤ ካህኑም ከበደሉ መሥዋዕት ደም ወስዶ የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት ያስነካዋል። 26ካህኑም ከዘይቱ በግራ እጁ መዳፍ ላይ ያፈስሳል። 27ካህኑም በግራ እጁ መዳፍ ላይ ያለውን ዘይት በቀኝ ጣቱ ሰባት ጊዜ በጌታ ፊት ይረጨዋል። 28ካህኑም በእጁ መዳፍ ላይ ካለው ዘይት የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት፥ የበደልም መሥዋዕት ደም ባረፈበት ስፍራ ላይ ያስነካዋል። 29በጌታ ፊት እንዲያስተሰርይለት ካህኑ በእጁ መዳፍ ላይ የተረፈውን ዘይት በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያደርገዋል። 30ለመግዛትም አቅሙ የሚፈቅድለትን ያህል ከዋኖሶች ወይም ከርግብ ግልገሎች አንዱን ያቀርባል፤ 31#ዘሌ. 1፥14-17፤ 5፥7-10።አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሌላውንም ከእህል ቁርባን ጋር ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባል፥ ካህኑም ለሚነጻው ሰው በጌታ ፊት ያስተሰርይለታል።
32“ለመንጻቱ የሚቀርበውን ነገር መግዛት አቅሙ ለማይፈቅድለት የለምጽ ደዌ ላለበት ሰው ሕጉ ይህ ነው።”
33ጌታም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ 34#ዘኍ. 12፥9-15፤ 2ነገ. 15፥4-5፤ 2ዜ.መ. 26፥16-21።“እኔ ወደምሰጣችሁ ርስት ወደ ከነዓን ምድር በገባችሁ ጊዜ፥ በምትወርሱአት ምድር በአንድ ቤት ውስጥ የለምጽ ደዌ ባኖር፥ 35የቤቱ ባለቤት መጥቶ ካህኑን፦ ‘ደዌ የሚመስል ነገር በቤቴ ውስጥ ያለ ይመስለኛል’ ብሎ ይንገረው። 36ካህኑም በቤቱ ውስጥ ያለው ዕቃ ሁሉ እንዳይረክስ፥ እርሱ ደዌውን ለማየት ወደ ቤቱ ከመግባቱ በፊት፥ ቤቱን ባዶ እንዲያደርጉት ያዝዛል፤ ከዚያም በኋላ ካህኑ ቤቱን ለማየት ይገባል። 37#ዘሌ. 13፥49።ደዌውንም ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው በቤቱ ግድግዳ ላይ አረንጓዴ ወይም ቀይ ሆኖ ቢዥጐረጐር፥ መልኩም ከግድግዳው ውጫዊ ገጽታ ዘልቆ ቢገባ፥ 38ካህኑ ከቤቱ ውስጥ ወደ ቤቱ በር ወጥቶ ሰባት ቀን ቤቱን ይዘጋዋል። 39ካህኑም በሰባተኛው ቀን ተመልሶ ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው በቤቱ ግድግዳ ላይ ቢሰፋ፥ 40ካህኑ ደዌ ያለባቸውን ድንጋዮች እንዲያወጡ፥ ከከተማውም ውጭ ወደ ረከሰው ስፍራ እንዲጥሉአቸው ያዝዛል። 41የቤቱንም ውስጥ ዙሪያውን ያስፍቀዋል፤ የፋቁትንም የምርጊቱን አፈር ከከተማው ውጭ ወደ ረከሰ ስፍራ ያፈስሱታል። 42በእነዚያም ድንጋዮች ስፍራ ሌሌች ድንጋዮችን አምጥተው ያገባሉ፤ ሌላም ጭቃ ወስደው ቤቱን ይመርጉታል።
43“ደዌውም ዳግም ቢመለስ፥ ድንጋዮቹም ከወጡ ቤቱም ከተፋቀና ከተመረገ በኋላ በቤቱ ውስጥ ቢሰፋ፥ 44ካህኑ ገብቶ ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው በቤቱ ውስት ቢሰፋ፥ በቤቱ ውስጥ ያለው እየሰፋ የሚሄድ የለምጽ ደዌ ነው፤ እርሱ ርኩስ ነው። 45ቤቱንም፥ ድንጋዮቹንም፥ እንጨቱንም፥ የቤቱንም ምርጊት ሁሉ ያፈርሳል፤ እነርሱንም ከከተማው ውጭ ወደ ርኩስ ስፍራ ያወጣል። 46#ዘሌ. 15፥10።በተዘጋበትም ጊዜ ሁሉ ወደ ቤቱ የሚገባ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። 47በቤቱም ውስጥ የሚተኛ ልብሱን ያጥባል፤ በቤቱም ውስጥ የሚበላ ልብሱን ያጥባል።
48 #
ዘሌ. 14፥2-9። “ካህኑም ገብቶ ቢያይ፥ እነሆም፥ ቤቱ ከተመረገ በኋላ ደዌው በቤቱ ውስጥ ባይሰፋ፥ ደዌው ስለ ጠፋ ካህኑ ቤቱን፦ ንጹሕ ነው ይለዋል። 49ቤቱንም ለማንጻት ሁለት ወፎች፥ የዝግባም እንጨት፥ ቀይ ግምጃም፥ ሂሶጵም ይወስዳል። 50አንደኛውንም ወፍ በሸክላ ዕቃ ውስጥ በምንጭ ውኃ ላይ ያርዳል። 51የዝግባውን እንጨት፥ ሂሶጱንም፥ ቀዩንም ግምጃ፥ በሕይወትም ያለውን ወፍ ወስዶ በታረደው ወፍ ደምና በምንጩ ውኃ ውስጥ ይነክራቸዋል፥ ቤቱንም ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። 52ቤቱንም በወፉ ደም፥ በምንጩም ውኃ፥ ሕይወትም ባለው ወፍ፥ በዝግባውም እንጨት፥ በሂሶጱም፥ በቀዩም ግምጃ ያነጻዋል። 53በሕይወትም ያለውን ወፍ ከከተማ ወጥቶ ወደ ተንጣለለው ሜዳ እንዲበር ይለቀዋል፤ ለቤቱም ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ንጹሕ ይሆናል።”
54“ይህ ሕግ ለሁሉም ዓይነት የለምጽ ደዌ፥ ለቈረቈርም፥ 55በልብስ ላይና በቤት ውስጥ ላለ የለምጽ ደዌ፥ 56ለእባጭም፥ ለብጉርም፥ ለቋቁቻም የሚሆን ነው። 57እንዲሁም አንድ ነገር በሚረክስና በሚነጻ ጊዜ ለማልከት የሚያስችል ነው። ይህ የለምጽ ደዌ ሕግ ነው።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 14: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ