መጽሐፈ ኢያሱ 24:1-25

መጽሐፈ ኢያሱ 24:1-25 መቅካእኤ

ኢያሱም የእስራኤልን ነገድ ሁሉ ወደ ሴኬም ሰበሰበ፥ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች አለቆቻቸውንም ፈራጆቻቸውንም ሹማምንቶቻቸውንም ጠራ። እነርሱም በጌታ ፊት ቆሙ። ኢያሱም ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አለ፦ “የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘አባቶቻችሁ፥ የአብርሃምና የናኮር አባት ታራ፥ አስቀድመው በወንዝ ማዶ ተቀመጡ፤ ሌሎችንም አማልክት አመለኩ። አባታችሁንም አብርሃምን ከወንዝ ማዶ ወስጄ በከነዓን ምድር ሁሉ መራሁት፤ ዘሩንም አበዛሁ፥ ይስሐቅንም ሰጠሁት። ለይስሐቅም ያዕቆብንና ዔሳውን ሰጠሁት፤ ለዔሳውም የሴይርን ተራራ ርስት አድርጌ ሰጠሁት፤ ያዕቆብም ልጆቹም ወደ ግብጽ ወረዱ። ሙሴንና አሮንንም ላክሁ፥ በመካከላቸውም እንዳደረግሁ ግብጽን ቀሠፍሁ፤ ከዚያም በኋላ እናንተን አወጣሁ። አባቶቻችሁንም ከግብጽ አወጣኋቸው፥ ወደ ባሕሩም ደረሳችሁ፤ ግብፃውያንም አባቶቻችሁን በሰረገሎችና በፈረሰኞች እስከ ኤርትራ ባሕር ድረስ አባረሩአቸው። ወደ ጌታም በጮኹ ጊዜ በእናንተና በግብፃውያን መካከል ጨለማ አደረገ፥ ባሕሩንም መለሰባቸው፥ አሰጠማቸውም፤ ዐይኖቻችሁም በግብጽ ያደረግሁትን አዩ፤ በምድረ በዳም ብዙ ጊዜ ተቀመጣችሁ። እኔም በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ተቀመጡበት ወደ አሞራውያን ምድር አመጣኋችሁ፤ ከእናንተም ጋር ተዋጉ፥ አሳልፌም በእጃችሁ ሰጠኋችሁ፥ ምድራቸውንም ወረሳችሁ፤ ከፊታችሁም አጠፋኋቸው። የሞዓብም ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ ተነሥቶ ከእስራኤል ጋር ተዋጋ፤ እንዲረግማችሁም የቢዖርን ልጅ በለዓምን ልኮ አስጠራው። እኔ ግን በለዓምን መስማት አልፈለግሁም፤ እርሱም ፈጽሞ ባረካችሁ፥ እኔም ከእጁ አዳንኋችሁ። ዮርዳኖስንም ተሻገራችሁ፥ ወደ ኢያሪኮም መጣችሁ፤ የኢያሪኮም ሰዎች፥ አሞራዊው፥ ፌርዛዊው፥ ከነዓናዊው፥ ኬጢያዊው፥ ጌርጌሳዊው፥ ኤዊያዊው፥ ኢያቡሳዊው ተዋጉአችሁ፤ አሳልፌም በእጃችሁ ሰጠኋቸው። በሰይፍህም በቀሥትህም ሳይሆን በፊታችሁም ተርብ ሰድጄ ሁለቱን የአሞራውያንን ነገሥታት ከፊታችሁ አሳደዳቸው። ያልደከማችሁበትንም ምድር፥ ያልሠራችኋቸውንም ከተሞች ሰጠኋችሁ፥ ተቀመጣችሁባቸውም፤ ካልተከላችኋቸውም ከወይንና ከወይራ በላችሁ።’ “እንግዲህ አሁን ጌታን ፍሩ፥ በፍጹም ቅንነትና ታማኝነት አገልግሉት፤ አባቶቻችሁም በወንዝ ማዶ በግብጽም ውስጥ ያመለኩአቸውን አማልክት ከእናንተ አርቁ፥ ጌታንም አምልኩ። ጌታንም ማገልገል ክፉ መስሎ ቢታያችሁ፥ አባቶቻችሁ በወንዝ ማዶ ሳሉ ያገለገሉአቸውን አማልክት ወይም በምድራቸው የተቀመጣችሁባቸውን የአሞራውያንን አማልክት ታገለግሉ እንደሆነ፥ የምታገለግሉትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን ጌታን እናገለግላለን።” ሕዝቡም መልሰው እንዲህ አሉ፦ “ጌታን ትተን ሌሎችን አማልክትን ማገልገል ከእኛ ይራቅ፤ እኛንና አባቶቻችንን ከባርነት ቤት ከግብጽ ምድር ያወጣን፥ በዓይናችንም ፊት እነዚያን ታላላቅ ተአምራት ያደረገ፥ በሄድንባትም መንገድ ሁሉ ባለፍንባቸውም አሕዛብ ሁሉ መካከል የጠበቀን፥ እርሱ ጌታ አምላካችን ነውና። ጌታ አሕዛብን ሁሉ፥ በምድሪቱ የተቀመጡትን አሞራውያን ከፊታችን አሳደደ፤ ስለዚህ እርሱ አምላካችን ነውና ጌታን እናገለግላለን።” ኢያሱም ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ “እርሱ ቅዱስ አምላክ ነውና፥ እርሱም ቀናተኛ አምላክ ነውና ጌታን ማገልገል አትችሉም፤ መተላለፋችሁንና ኃጢአታችሁን ይቅር አይልም። ጌታን ትታችሁ እንግዶችን አማልክት ብታመልኩ፥ መልካም ካደረገላችሁ በኋላ ተመልሶ ክፉ ነገር ያደርግባችኋል፥ ያጠፋችኋልም።” ሕዝቡም ኢያሱን፦ “እንዲህ አይሁን፤ ነገር ግን ጌታን እናገለግላለን” አሉት። ኢያሱም ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ “እንድታገለግሉት እናንተ ጌታን እንደ መረጣችሁ በራሳችሁ ላይ ምስክሮች ናችሁ፤” እነርሱም፦ “ምስክሮች ነን” አሉ። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “አሁን እንግዲህ በመካከላችሁ ያሉትን እንግዶች አማልክት አርቁ፥ ልባችሁንም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ ጌታ አዘንብሉ።” ሕዝቡም ኢያሱን፦ “ጌታ አምላካችንን እናገለግላለን፥ ድምፁንም እንሰማለን” አሉት። በዚያም ቀን ኢያሱ ከሕዝቡ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፥ በሴኬምም ሥርዓትና ፍርድ አደረገላቸው።