ኢያሱም ሸመገለ ዕድሜውም ስለ ገፋ አረጀ፤ ጌታም እንዲህ አለው፦ “አንተ ሸምግለሃል፥ ዕድሜህም ስለ ገፋ አርጅተሃል፤ ያልተወረሰ እጅግ ብዙ ምድር ገና ይቀራል፤ ሳይያዝ የቀረውም ምድር ይህ ነው፥ የፍልስጥኤማውያንና የጌሹራውያን አገር ሁሉ፥ በግብጽ ፊት ለፊት ካለው ከሺሖር ወንዝ ጀምሮ በሰሜን በኩል እስካለችው የከነዓናውያን ሆና እስከ ተቈጠረችው እስከ አቃሮን ዳርቻ ድረስ፥ የጋዛ፥ የአዛጦን፥ የአስቀሎና፥ የጌት፥ የአቃሮን፥ አምስቱ የፍልስጥኤማውያን ገዢዎች ናቸው፥ የኤዋውያን የሆኑትም እንዲሁ፥ በደቡብም በኩል የነዓናውያን ምድር ሁሉ፥ ለሲዶናውያንም የምትሆን መዓራ እስከ አሞራውያን ዳርቻ እስከ አፌቅ ድረስ፥ የጌባላውያንም ምድር፥ በፀሐይም መውጫ በኩል ከአርሞንዔም ተራራ በታች ካለችው በኣልጋድ ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ ድረስ ያለችው ሊባኖስ ሁሉ፥ በተራራማውም አገር የሚኖሩትን ሁሉ ከሊባኖስ ጀምሮ እስከ ማሴሮን ድረስ ሲዶናውያን ሁሉ፥ እኔ ራሴ እነዚህን ከእስራኤል ልጆች ፊት አባርራቸዋለሁ፤ እንዳዘዝሁህም ምድራቸውን ለእስራኤል ብቻ ርስት አድርገህ አካፍላቸው። እንግዲህ አሁን ይህን ምድር ለዘጠኙ ነገድ ለምናሴም ነገድ እኩሌታ ርስት አድርገህ ክፈለው።” የጌታ ባርያ ሙሴ እንደሰጣቸው ከሌሎቹ የምናሴ ነገድ እኩሌታ ጋር የሮቤልና የጋድ ልጆች በምሥራቅ በኩል በዮርዳኖስ ማዶ ሙሴ የሰጣቸውን ርስታቸውን ተቀበሉ። በአርኖን ሸለቆ ዳር ካለችው ከአሮዔር፥ በሸለቆውም መካከል ካለችው ከተማ ጀምሮ የሜድባን ሜዳ ሁሉ እስከ ዲቦን ድረስ፥ በሐሴቦንም የነገሠ የአሞራውያን ንጉሥ የሴዎን ከተሞች ሁሉ እስከ አሞን ልጆች ዳርቻ ድረስ፥ ገለዓድንም፥ የጌሹራውያንንና የማዕካታውያንን ግዛት ሁሉ፥ የአርሞንዔምንም ተራራ ሁሉ፥ ባሳንንም ሁሉ እስከ ሰልካ ድረስ፥ በባሳን የነበረውን በአስታሮትና በኤድራይ የነገሠውን የዐግን መንግሥት ሁሉ፤ እርሱም ብቻ ከራፋይም የቀረ ነበረ፤ እነዚህንም ሙሴ ድል አድርጎ አስወጣቸው። የእስራኤል ልጆች ግን ጌሹራውያንንና ማዕካታውያንን አላስወጡም፤ እስከ ዛሬም ድረስ ጌሹርና ማዕካት በእስራኤል መካከል ይኖራሉ። ለሌዊ ነገድ ግን ርስት አልሰጠም፤ እርሱ እንደ ተናገራቸው እንዲሁ ለእስራኤል አምላክ ለጌታ በእሳት የሚቀርበው መሥዋዕት ርስታቸው ነው።
መጽሐፈ ኢያሱ 13 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ኢያሱ 13:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች