መጽሐፈ ኢያሱ 10:7-14

መጽሐፈ ኢያሱ 10:7-14 መቅካእኤ

ኢያሱም ከእርሱም ጋር የነበሩ ተዋጊዎች ሁሉ ጽኑዓን ኃያላኑም ሁሉ ከጌልገላ ወጡ። ጌታም ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼአቸዋለሁና አትፍራቸው፤ ከእነርሱም አንድም ሰው የሚቋቋምህ የለም።” ኢያሱም ከጌልገላ ሌሊቱን ሁሉ ገሥግሦ በድንገት መጣባቸው። ጌታም በእስራኤል ፊት አስደነገጣቸው፤ በገባዖንም በጽኑ ውግያ ድል አደረጓቸው፥ በቤትሖሮንም ዐቀበት በሆነው መንገድ ላይ አሳደዳቸው፥ እስከ ዓዜቃና እስከ መቄዳ ድረስ መታቸው። ከእስራኤልም ልጆች ፊት እየሸሹ የቤትሖሮንን ቁልቁለት በመውረድ ላይ ሳሉ፥ ዓዜቃ እስኪደርሱ ድረስ ጌታ ከሰማይ ታላላቅ ድንጋይ አወረደባቸውና ሞቱ፤ የእስራኤል ልጆች በሰይፍ ከገደሉአቸው ይልቅ በበረዶ ድንጋይ የሞቱት በለጡ። ጌታም በእስራኤል ልጆች እጅ አሞራውያንን አሳልፎ በሰጠ ቀን ኢያሱ ለጌታ እንዲህ ብሎ ተናገረ፤ የእስራኤልም ልጆች እያዩ እንዲህ አለ፦ “በገባዖን ላይ ፀሐይ ትቁም፥ በኤሎንም ሸለቆ ጨረቃ፤” ሕዝቡም ጠላቶቻቸውን እስኪበቀሉ ድረስ ፀሐይ ቆመች፥ ጨረቃም ዘገየች። ይህስ በያሻር መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? ፀሐይም በሰማይ መካከል ጸንታ ቆመች፥ አንድ ቀንም ሙሉ ያህል ለመግባት አልቸኰለችም። ጌታ ለእስራኤል ይዋጋ ነበረና ጌታ የሰውን ቃል የሰማበት እንደዚያ ያለ ቀን ከዚያም በፊት ከዚያም በኋላ አልነበረም።