እንዲህም ሆነ፤ የጌታ ባርያ ሙሴ ከሞተ በኋላ ጌታ የሙሴን አገልጋይ የነዌን ልጅ ኢያሱን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ባርያዬ ሙሴ ሞቷል፤ እንግዲህ አሁን አንተና ይህ ሕዝብ ሁሉ ተነሥታችሁ ለእስራኤል ልጆች ወደምሰጣቸው ምድር ይህን ዮርዳኖስ ተሻገሩ። ለሙሴ እንደ ነገርሁት የእግራችሁ ጫማ የሚረግጠውን ቦታ ሁሉ ለእናንተ ሰጥቼአለሁ። ከምድረ በዳው ከዚህም ከሊባኖስ ጀምሮ እስከ ታላቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ የኬጥያውያን ምድር ሁሉ፥ እስከ ፀሐይ መግቢያ እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ግዛታችሁ ይሆናል። በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ማንም አይቋቋምህም፤ ከሙሴ ጋር እንደ ነበርሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ አልጥልህም፥ አልተውህምም። ለአባቶቻቸው፦ እሰጣችኋለሁ ብዬ የማልሁላቸውን ምድር ለዚህ ሕዝብ ታወርሳለህና ጽና፥ አይዞህ። ነገር ግን ጽና፥ እጅግም በርታ፤ ባርያዬ ሙሴ ያዘዘህን ሕግ ሁሉ ጠብቅ፥ አድርገውም፤ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲከናወንልህ ከእርሱ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል። የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአንደበትህ አይለይ፥ ነገር ግን በእርሱ ውስጥ የተጻፈውን ሁሉ እንድትጠብቅና እንድታደርገው በቀንም በሌሊትም አሰላስለው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቃናልሃል ይከናወንልሃልም። በምትሄድበት ሁሉ ጌታ አምላክህ ከአንተ ጋራ ነውና ጽና፥ አይዞህ፥ አትፍራ፥ አትደንግጥ ብዬ አላዘዝሁህምን?” ኢያሱም የሕዝቡን አለቆች እንዲህ ብሎ አዘዘ፦ “በሰፈሩ መካከል እለፉ፥ ሕዝቡንም እንዲህ ብላችሁ እዘዙ፦ ‘ጌታ አምላካችሁ ርስት አድርጎ ወደሚሰጣችሁ ምድር በሦስት ቀን ውስጥ ይህን ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ልትወርሱአት ትገቡባታላችሁና ስንቃችሁን አዘጋጁ።’ ” ኢያሱም የሮቤልን ልጆች የጋድንም ልጆች የምናሴንም ነገድ እኩሌታ እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ “የጌታ ባርያ ሙሴ እንዲህ ብሎ ያዘዛችሁን ቃል አስታውሱ፦ ‘ጌታ አምላካችሁ ያሳርፋችኋል፥ ይህችንም ምድር ይሰጣችኋል።’ ሚስቶቻችሁና ልጆቻችሁ ከብቶቻችሁም ሙሴ በዮርዳኖስ ማዶ በሰጣችሁ ምድር ይቀመጡ፤ ነገር ግን እናንተ፥ ጽኑዓን ኃያላን ሁሉ፥ ተሰልፋችሁ በወንድሞቻችሁ ፊት ተሻገሩ፥ እርዱአቸውም፥ ጌታ እናንተን እንዳሳረፋችሁ ወንድሞቻችሁን እስኪያሳርፍ ድረስ፥ እነርሱም ደግሞ ጌታ አምላካችሁ የሚሰጣቸውን ምድር እስኪወርሱ ድረስ፤ ከዚያም በኋላ የጌታ ባርያ ሙሴ በፀሐይ መውጫ ወደ ሰጣችሁ ወደ ርስታችሁ ምድር ትመለሳላችሁ ትወርሱዋታላችሁም።” እነርሱም ለኢያሱ እንዲህ ብለው መለሱለት፦ “ያዘዝኸንን ነገር ሁሉ እናደርጋለን ወደምትልከንም ስፍራ ሁሉ እንሄዳለን።
መጽሐፈ ኢያሱ 1 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ኢያሱ 1:1-16
6 ቀናት
በዚህ የ6 ቀን ጥናት ውስጥ ፍርሃት፣ ግራ መጋባትና ጭንቀትን ለማስወገድ በሕይወታችን ውስጥ የእግዚአብሔር መኖር ምን ያህል ማድረግ እንደሚችል እናያለን። ከእግዚአብሔር ጋር ጊዜ በማሳለፍና ከቃሉ በመማር እነዚህን ተግዳሮቶች እንዴት ማሸነፍ እንደምንችል፣ ትኩረታችንን እንዴት እንደምናስተካክልና አስተሳሰባችንን እንደምንለውጥ እናያለን።
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች