ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል ነበረ፤ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት። በእነዚህም ውስጥ ብዙ ድኩማን፥ ዐይነ ሥውሮች፥ አንካሶችም ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ሰዎች ይተኙ ነበር። አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውሃውን ያናውጥ ነበርና፤ እንግዲህ ከውሃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ የገባ ከማናቸው ካለበት ደዌ ይፈወስ ይሆን ነበር። በዚያም ከሠላሳ ስምንት ዓመት ጀምሮ የታመመ አንድ ሰው ነበረ፤ ኢየሱስ ይህን ሰው ተኝቶ ባየ ጊዜ፥ እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ “ልትድን ትወዳለህን?” አለው። ሕመምተኛውም “ጌታ ሆይ! ውሃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም፤ ነገር ግን እኔ በመምጣት ላይ እያለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል፤” ብሎ መለሰለት። ኢየሱስ “ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ፤” አለው። ወዲያውም ሰውዬው ዳነ፤ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ። ያም ቀን ሰንበት ነበረ። ስለዚህ አይሁድ የተፈወሰውን ሰው “ሰንበት ነው፥ አልጋህንም ልትሸከም አልተፈቀደልህም፤” አሉት። እርሱ ግን “ያዳነኝ ያ ሰው ‘አልጋህን ተሸክመህ ሂድ፤’ አለኝ፤” ብሎ መለሰላቸው። እነርሱም “‘አልጋህን ተሸክመህ ሂድ፤’ ያለህ ሰው ማን ነው?” ብለው ጠየቁት። ዳሩ ግን የተፈወሰው ሰው ማን እንደሆነ አላወቀም፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ፈቀቅ ብሎ ስለ ነበርና፥ በዚያ ስፍራ ብዙ ሰዎች ሰለ ነበሩ ነው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በቤተ መቅደስ አገኘውና “እነሆ፥ ድነሃል፤ ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ፤” አለው። ሰውዬው ሄዶ ያዳነው ኢየሱስ እንደሆነ ለአይሁድ ነገረ። ስለዚህም አይሁድ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር፤ በሰንበት ይህን አድርጎ ነበርና። ኢየሱስ ግን “አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል፤ እኔም ደግሞ እሠራለሁ፤” ብሎ መለሰላቸው። እንግዲህ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ደግሞ እራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ “እግዚአብሔር አባቴ ነው፤” ስላለ፥ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ፤ እንዲህም አላቸው “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከእራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና። አብ ወልድን ይወዳልና፤ የሚያደርገውንም ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ትደነቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራ ያሳየዋል። አብ ሙታንን እንደሚያስነሣቸው፥ ሕይወትም እንደሚሰጣቸው፥ እንዲሁ ወልድ ደግሞ ለሚወዳቸው ሕይወትን ይሰጣቸዋል። አብ ከቶ በማንም ላይ አይፈርድም፤ ይልቁንም፥ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው። ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ ነው፤ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም። “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ። አብ በእራሱ ሕይወት እንዳለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ በእራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና። የሰው ልጅም ስለ ሆነ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን ሰጠው። በዚህ አታድንቁ፤ በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና። “እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ፤ ፍርዴም ቅን ነው፤ የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና።
የዮሐንስ ወንጌል 5 ያንብቡ
ያዳምጡ የዮሐንስ ወንጌል 5
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ወንጌል 5:1-30
9 ቀናት
እያንዳንዳቸው እየሱስ ክርስቶስ የህያው የእግዛብሔር ልጅ መሆኑን መልካም የምስራች ዜናን ያበስሩ ነበር። ይህ አጭር ቪዲዮ የኢሱስ ክርስቶስ የእያንዳንዱን ቀን ቁልፍ ተአምራትን በምሳሌ ይገልፃል።
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች