የዮሐንስ ወንጌል 3:5-21

የዮሐንስ ወንጌል 3:5-21 መቅካእኤ

ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ሰው ከውሃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት አይችልም። ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው። ዳግመኛ መወለድ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አትደነቅ። ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፤ ድምፁንም ትሰማለህ፤ ነገር ግን ከወዴት እንደመጣ ወዴትም እንደሚሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስም የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው።” ኒቆዲሞስ መልሶ “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” አለው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው “አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህንን አታውቅምን? እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፤ የእኛንም ምስክርነት አትቀበሉትም። ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ? ከሰማይም ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፤ እርሱም የሰው ልጅ ነው። ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ የሰው ልጅም መሰቀል ይገባዋል። በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት ይኖረው ዘንድ። “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና። በእርሱ የሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ ከወዲሁ ተፈርዶበታል። ፍርዱም ይህ ነው፥ ብርሃንም ወደ ዓለም መጣ፤ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ። ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፤ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር መከናወኑ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።”