የዮሐንስ ወንጌል 11:1-32

የዮሐንስ ወንጌል 11:1-32 መቅካእኤ

አንድ ሰው ታሞ ነበር፤ እርሱም እንደ ማርያምና እንደ እኅትዋ ማርታ ከቢታንያ የነበረው አልዓዛር ነው። ማርያም ጌታን ሽቱ የቀባችው፥ እግሩንም በጠጉርዋ ያበሰችው ስትሆን፤ የታመመውም አልዓዛር ወንድምዋ ነበር። ስለዚህም እኅቶቹ “ጌታ ሆይ! እነሆ የምትወደው ታሞአል፤” ብለው ወደ እርሱ ላኩበት። ኢየሱስም ሰምቶ “ይህ ሕመም ለሞት አይሰጥም፤ ይልቁንም ለእግዚአብሔር ክብር መገለጫ ነው፤ የእግዚአብሔር ልጅ በእርሱ ይከብር ዘንድ ነው” አለ። ኢየሱስም ማርታንና እኅትዋን እንዲሁም አልዓዛርን ይወድ ነበር። እንደ ታመመም በሰማ ጊዜ ያንጊዜ በነበረበት ስፍራ ሁለት ቀን ዋለ፤ ከዚህም በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ “ወደ ይሁዳ እንደገና እንሂድ፤” አላቸው። ደቀመዛሙርቱ “መምህር ሆይ! አይሁድ ከጥቂት ጊዜ በፊት ሊወግሩህ ይፈልጉ ነበር፤ በድጋሚ ወደዚያ ትሄዳለህን?” አሉት። ኢየሱስም መልሶ “በቀን ውስጥ ዐሥራ ሁለት ሰዓት ይገኙ የለምን? በቀን የሚመላለስ የዚህን ዓለም ብርሃን ያያልና አይሰናከልም፤ በሌሊት የሚመላለስ ቢኖር ግን ብርሃን በእርሱ ስለ ሌለ ይሰናከላል፤” አላቸው። ይህንንም ከተናገረ በኋላ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ፤” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም “ጌታ ሆይ! ተኝቶ እንደ ሆነስ ይድናል፤” አሉት። ኢየሱስ ግን ስለ ሞቱ ነበር የተናገረው፤ እነርሱ ግን ስለ እንቅልፍ የተናገረ መሰላቸው። እንግዲህ ያንጊዜ ኢየሱስ በግልጥ “አልዓዛር ሞተ፤ እናንተ እንድታምኑም በዚያ ባለመኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ወደ እርሱ እንሂድ፤” አላቸው። ዲዲሞስ የሚሉትም ቶማስ ለሌሎቹ ደቀ መዛሙርት “ከእርሱ ጋር እንሞት ዘንድ እኛም እንሂድ፤” አለ። ኢየሱስም በመጣ ጊዜ አልዓዛር ከተቀበረ አራት ቀን ሆኖት ነበር። ቢታንያም ዐሥራ አምስት ምዕራፍ ያህል ለኢየሩሳሌም ቅርብ ነበረች። ከአይሁድም ብዙዎች ስለ ወንድማቸው ሊያጽናኑአቸው ወደ ማርታና ወደ ማርያም መጥተው ነበር። ማርታም ኢየሱስ እንደመጣ በሰማች ጊዜ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ተቀምጣ ነበር። ማርታም ኢየሱስን “ጌታ ሆይ! አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር፤ አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚሰጥህ አውቃለሁ፤” አለችው። ኢየሱስም “ወንድምሽ ይነሣል፤” አላት። ማርታም “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንደሚነሣ አውቃለሁ፤” አለችው። ኢየሱስም “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነና በእኔ የሚያምን ሁሉ ለዘለዓለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽኝ?” አላት። እርሷም “አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆንህ እኔ አምናለሁ” አለችው። ይህንም ብላ ሄደች፤ እኅትዋንም ማርያምን በስውር ጠርታ “መምህር መጥቷል፤ እየጠራሽም ነው፤” አለቻት። እርሷም በሰማች ጊዜ ፈጥና ተነሣች፥ ወደ እርሱም መጣች፤ ኢየሱስም ማርታ እርሱን በተቀበለችበት ስፍራ ነበረ እንጂ ገና ወደ መንደሩ አልገባም ነበር። ከእርሷ ጋር በቤት ሲያጽናኑአት የነበሩ አይሁድም፥ ማርያም ፈጥና እንደ ተነሣችና እንደ ወጣች ባዩ ጊዜ፥ ወደ መቃብር ሄዳ በዚያ ልታለቅስ መስሎአቸው ተከተሉአት። ማርያምም ኢየሱስ ወዳለበት መጥታ ባየችው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቃ “ጌታ ሆይ! አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር፤” አለችው።