“እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ወደ በጎች በረት በበሩ ሳይሆን የማይገባ በሌላ መንገድ የሚገባ እርሱ ሌባና ወንበዴ ነው፤ በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው። ለእርሱ በር ጠባቂው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰሙታል፤ የእራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ ይወስዳቸዋል። የእራሱንም ሁሉ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል፤ ከሌላው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም፤ የሌሎቹን ድምፅ አያውቁምና።” ኢየሱስ ይህንን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን የነገራቸው ምን እንደሆነ አላስተዋሉም። ኢየሱስም ደግሞ አላቸው “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ እኔ የበጎች በር ነኝ። ከእኔ በፊት የመጡ ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ ዳሩ ግን በጎቹ አልሰሙአቸውም። በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል፤ ይገባልም፤ ይወጣልም፤ መሰማሪያም ያገኛል። ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድና ሊያጠፋ እንጂ ለሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወትን እንዲያገኙ፥ የተትረፈረፈ ሕይወትን እንዲያገኙ መጣሁ፤ መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ አሳልፎ ይሰጣል። እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑት ተቀጣሪው ግን፥ ተኩላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኩላም ይነጥቃቸዋል፤ በጎቹንም ይበትናቸዋል። ተቀጣሪ ስለሆነ፥ ለበጎቹም ስለማይገደው ይሸሻል። መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ የእራሴን በጎች አውቃለሁ፤ የእራሴም በጎች ያውቁኛል። አብም እንደሚያውቀኝ፥ እኔም አብን እንደማውቀው፤ ነፍሴንም ስለ በጎቼ አሳልፌ እሰጣለሁ። ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ማምጣት ይገባኛል፤ ድምፄንም ይሰማሉ፤ አንድም መንጋ ይሆናሉ፤ እረኛውም አንድ። መልሼ ለመውሰድ ነፍሴን አሳልፌ ስለምሰጥ አብ ይወደኛል። እኔ ነፍሴን በፈቃዴ አሳልፌ እሰጣለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም። አሳልፌ ለመስጠት ሥልጣን አለኝ፤ መልሼ ለመውሰድም ሥልጣን አለኝ፤ ይህችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ።” ከእነኚህ ቃላት የተነሣ በአይሁድ መካከል እንደገና መለያየት ሆነ። ከእነርሱም ብዙዎች “ጋኔን አለበት፤ አብዶአልም፤ ለምንስ ትሰሙታላችሁ?” አሉ። ሌሎችም “ይህ ጋኔን ያለበት ሰው ቃል አይደለም፤ ጋኔን የዐይነ ሥውሮችን ዐይን ሊከፍት ይችላልን?” አሉ። በኢየሩሳሌምም የመቅደስ መታደስ በዓል ሆነ፤ ወቅቱም የብርድ ጊዜ ነበር። ኢየሱስም በመቅደስ፥ በሰሎሞን ታዛ ይመላለስ ነበር። አይሁድም እርሱን ከብበው “እስከ መቼ ድረስ በጥርጣሬ ታቆየናለህ? አንተ ክርስቶስ ከሆንህ በግልጥ ንገረን፤” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ነገርኋችሁ፤ ነገር ግን አታምኑም፤ እኔ በአባቴ ስም የማደርጋቸው ሥራዎች ስለ እኔ ይመሰክራሉ፤ እናንተ ግን ከበጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም። በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔም አውቃቸዋለሁ፤ ይከተሉኝማል፤ እኔም የዘለዓለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘለዓለምም አይጠፉም፤ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም። የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፤ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም። እኔና አብ አንድ ነን።” አይሁድ ሊወግሩት ደግመው ድንጋይ አነሡ። ኢየሱስ “ከአባቴ ብዙ መልካም ሥራ አሳየኋችሁ፤ ከእነርሱ ስለ የትኛው ሥራ ትወግሩኛላችሁ?” ብሎ መለሰላቸው። አይሁድም “ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም፤ ስለ ስድብ እንጂ፤ ይልቁንም አንተ ሰው ሆነህ ሳለህ እራስህን አምላክ ስለ ማድረግህ ነው” ብለው መለሱለት። ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ “እኔ ‘አማልክት ናችሁ አልሁ፤’ ተብሎ በሕጋችሁ ተጽፎ የለምን? መጽሐፉ ሊሻር አይቻልምና እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን አማልክት ካላቸው፥ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ አብ የቀደሰውንና ወደ ዓለም የላከውን እናንተ ‘ትሳደባለህ፤’ ትሉታላችሁን? እኔ የአባቴን ሥራ የማልሠራ ከሆነ አትመኑኝ፤ የምሠራ ከሆነ ግን፥ እኔን እንኳን ባታምኑ፥ አብ በእኔ እንደሆነ እኔም በአብ እንደሆንሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ሥራውን እመኑ።” ደግመኛም ሊይዙት ፈለጉ፤ ከእጃቸውም አምልጦ ሄደ። ዮሐንስም በመጀመሪያ ያጠምቅበት ወደነበረው ስፍራ፥ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ፥ እንደገና ሄደ፤ በዚያም ተቀመጠ። ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጥተው “ዮሐንስ አንድ ምልክት እንኳን አላደረገም፤ ነገር ግን ዮሐንስ ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት ነበረ፤” አሉ። በዚያም ብዙዎች በእርሱ አመኑ።
የዮሐንስ ወንጌል 10 ያንብቡ
ያዳምጡ የዮሐንስ ወንጌል 10
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ወንጌል 10:1-42
9 ቀናት
ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማስረዳት ተግባራዊ እና የፈጠራ ታሪኮችን ተጠቅሟል። አንድ አጭር ቪዲዮ ዘጠኙን ክፍሎች ያሉት እቅድ በእያንዳንዱ ቀን ከኢየሱስ ትምህርቶች አንዱን ያሳያል።
ጌታ ኢየሱስ ስለ አገልግሎቱ ሲናገር ዓላማው ለሰዎች የዘላለም ሕይወት መስጠት እንደሆነ ተናግሯል። “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ” (ዮሐ. 3፡16)። ይህ የዘላለም ሕይወት ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ የዘላለም ሕይወት ምን እንደሚል እንመልከት።
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች