በዚያን ዘመን፥ ይላል ጌታ፥ ለእስራኤል ወገኖች ሁሉ አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል። ጌታ እንዲህ ይላል፦ እስራኤል ማረፊያ ሊሻ በሄደ ጊዜ ከሰይፍ የተረፈው ሕዝብ በምድረ በዳ ሞገስ አገኘ። ጌታም ከሩቅ ተገለጠልኝ እንዲህም አለኝ፦ “በዘለዓለም ፍቅር ወድጄሻለሁ፤ ስለዚህ በጽኑ ፍቅር ሳብሁሽ። የእስራኤል ድንግል ሆይ! እንደገና እሠራሻለሁ አንቺም ትሠሪያለሽ፤ እንደገናም ከበሮሽን አንሥተሽ ሐሤት በሚያደርጉ ዘፋኞች ሽብሸባ እያሸበሸብሽ ትወጫለሽ። እንደገናም በሰማርያ ተራሮች ላይ ወይንን በወይን እርሻዎች ትተክዪአለሽ፤ አትክልተኞች ይተክላሉ እነርሱም በፍሬው ይደሰታሉ። በኤፍሬምም ተራሮች ላይ ያሉ ጠባቂዎች፦ ‘ተነሡ፥ ወደ ጽዮን ወደ አምላካችን ወደ ጌታ እንውጣ’ ብለው የሚጣሩበት ቀን ይመጣልና።” ጌታ እንዲህ ይላልና፦ ስለ ያዕቆብ በደስታ ዘምሩ ስለ አሕዛብም አለቆች እልል በሉ፤ አውጁ፥ አመስግኑ፦ ጌታ ሆይ! ሕዝብህን የእስራኤልን ትሩፍ አድን በሉ። እነሆ፥ ከሰሜን አገር አመጣቸዋለሁ፤ ከምድርም ዳርቻ እሰበስባቸዋለሁ፤ በመካከላቸውም ዓይነ ስውርና አንካሳው ያረገዘችና ምጥ የያዛትም በአንድነት ይሆናሉ፤ ታላቅ ጉባኤ ሆነው ወደዚህ ይመለሳሉ። በልቅሶ ይወጣሉ፤ እኔንም በመማፀናቸው እየመራሁ እመልሳቸዋለሁ፤ በወንዝ ዳር በቅን መንገድ አስኬዳቸዋለሁ፤ በእርሱም አይሰናከሉም፤ እኔ ለእስራኤል አባት ነኝና፥ ኤፍሬምም በኩሬ ነውና። አሕዛብ ሆይ! የጌታን ቃል ስሙ፥ በሩቅም ላሉ ደሴቶች አውጁ፦ “እስራኤልን የበተነ እርሱ ይሰበስበዋል፥ እረኛም መንጋውን እንደሚጠብቅ ይጠብቀዋል” በሉ። ጌታ ያዕቆብን ተቤዥቶታል፥ ከበረታበትም እጅ አድኖታል። ይመጣሉ በጽዮንም ተራራ ላይ ሆነው እልል ይላሉ፤ ስለ ጌታም በጎነቱ፥ ስለ እህሉና ስለ ወይን ጠጁ፥ ስለ ዘይቱም፥ ስለ በጎቹና ስለ ከብቶቹ በሐሤት ይሞላሉ፤ ነፍሳቸውም ውኃ ጠጥታ እንደ ረካች ገነት ትሆናለች፥ ከእንግዲህም ወዲህ አያዝኑም። በዚያን ጊዜም ድንግሊቱ በሽብሸባ ትደሰታለች፥ ጉልማሶቹና ሽማግሌዎቹም በአንድ ላይ ደስ ይላቸዋል፤ ልቅሶአቸውንም ወደ ደስታ እለውጣለሁ፥ አጽናናቸዋለሁም፥ ከኀዘናቸውም ደስ አሰኛቸዋለሁ። የካህናቱንም ነፍስ በብዛት አረካታለሁ ሕዝቤም በጎነቴን ይጠግባል፥ ይላል ጌታ። ጌታ እንዲህ ይላል፦ “የዋይታና የመራራ ልቅሶ ድምፅ በራማ ተሰማ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፤ የሉምና ስለ ልጆችዋ መጽናናትን እንቢ አለች።” ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ድምፅሽን ከልቅሶ ዓይንሽንም ከእንባ ከልክዪ፤ ለሥራሽ የሚከፈልሽ ዋጋ ይሆናልና፥ ከጠላትም ምድር ይመለሳሉ፥ ይላል ጌታ። ለወደፊት ላለሽ ጊዜ ተስፋ አለሽ፥ ይላል ጌታ፥ ልጆችሽም ወደ ግዛታቸው ይመለሳሉ። በእውነት ኤፍሬም ሲያለቅስ ሰማሁ፦ ‘ቀጣኸኝ እኔም እንዳልተገራ ወይፈን ተቀጣሁ፤ አንተ ጌታ አምላኬ ነህና መልሰኝ እኔም እመለሳለሁ። ከተመለስሁ በኋላ ተጸጸትሁ፥ ከተገሠጽሁም በኋላ በኀዘን ጭኔን ጸፋሁ፤ የብላቴንነቴንም ስድብ ተሸክሜአለሁና አፈርሁ ተዋረድሁም።’ በእውነት ኤፍሬም የተወደደ ልጄ ነውን? ወይስ ደስ የምሰኝበት ሕፃን ነውን? በእርሱ ላይ በተናገርሁ ቍጥር አሁንም ድረስ በትክክል አስታውሰዋለሁ፤ ስለዚህ አንጀቴ ታወከችለት ርኅራኄም እራራለታለሁ፥ ይላል ጌታ። “ለራስሽ የመንገድ ምልክት አድርጊ፥ መንገድንም የሚመሩ ዓምዶችን ትከዪ፥ የሄድሽበትን መንገድ ዐውራ ጐዳናውን ልብ አድርገሽ ተመልከቺ፤ አንቺ የእስራኤል ድንግል ሆይ! ተመለሺ፥ ወደ እነዚህም ወደ ከተሞችሽ ተመለሺ። አንቺ ከዳተኛ ልጅ ሆይ! እስከ መቼ ታመነቻለሽ? ጌታ በምድር ላይ አዲስ ነገር ፈጥሮአልና ሴት ወንድን ትከብባለች።”
ትንቢተ ኤርምያስ 31 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኤርምያስ 31:1-22
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች