ትንቢተ ኤርምያስ 15

15
ቅጣት አይቀሬ መሆኑ
1 # ዘፀ. 32፥11-14፤ ዘኍ. 14፥13-19፤ 1ሳሙ. 7፥5-9። ጌታም እንደዚህ አለኝ፦ “ሙሴና ሳሙኤል በፊቴ ቢቆሙም እንኳ ልቤ ወደዚህ ሕዝብ አያዘነብልም፤ ከፊቴ አስወጣቸው፤ ይሂዱ። 2#ራእ. 13፥10።እነርሱም፦ ‘ወዴት እንውጣ?’ ቢሉህ፥ አንተ፦ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘ለሞት የሆነ ወደ ሞት፥ ለሰይፍም የሆነ ወደ ሰይፍ፥ ለራብም የሆነ ወደ ራብ፥ ለምርኮም የሆነ ወደ ምርኮ’ ትላቸዋለህ። 3ሰይፍን ለመግደል፥ ውሾችንም ለመጐተት፥ የሰማያትንም ወፎች የምድርንም አራዊት ለመብላትና ለማጥፋት፥ ዐራቱን ዓይነት ጥፋት ልኬባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ። 4#2ነገ. 21፥1-16፤ 2ዜ.መ. 33፥1-9።የይሁዳም ንጉሥ የሕዝቅያስ ልጅ ምናሴ በኢየሩሳሌም ስላደረገው ሁሉ፥ በምድር መንግሥታት ሁሉ ዘንድ ለድንጋጤ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ።
5“ኢየሩሳሌም ሆይ! የሚራራልሽ ማን ነው? የሚያዝንልሽስ ማን ነው? ወይስ ስለ ደኅንነትሽ ቆም ብሎ የሚጠይቅ ማነ ነው? 6አንቺ እኔን ትተሺኛል፥ ይላል ጌታ፥ ወደ ኋላሽም ተመልሰሻል፤ ስለዚህ እጄን በአንቺ ላይ ዘርግቼ አጥፍቼሻለሁ፤ ይቅርታን ከማድረግ ደክሜአለሁ። 7በምድሪቱም ደጆች ውስጥ በመንሽ አበጥሬአቸዋለሁ፤ የወላድ መካን አድርጌአቸዋለሁ፥ ሕዝቤንም አጥፍቼአለሁ፤ ከመንገዳቸውም አልተመለሱም። 8መበለቶቻቸውም ከባሕር አሸዋ ይልቅ በዝተውብኛል፤ በብላቴኖች እናት ላይ በቀትር ጊዜ አጥፊውን አምጥቻለሁ፤ ጣርንና ድንጋጤን በድንገት አምጥቼባታለሁ። 9ሰባት የወለደች ደክማለች፥ ነፍስዋንም አውጥታለች፤ ቀን ገና ሳለ ፀሐይዋ ገብታባታለች፤ አፍራለች ተዋርዳለችም፤ የተረፉትንም በጠላቶቻቸው ፊት ለሰይፍ አሳልፌ እሰጣለሁ፥ ይላል ጌታ።”
ነቢዩ ኤርምያስ ዳግመኛ ማጉረምረሙ እና ጌታ ማጽናናቱ
10እናቴ ሆይ፥ ወዮልኝ! ለምድር ሁሉ የሙግትና የጥል ሰው የሆንሁትን ወለድሽኝ፤ ለማንም አላበደርሁም፥ ማንም ለእኔ አላበደረም፥ ነገር ግን ሁሉ ይረግመኛል። 11ጌታ እንዲህ አለ፦ በእውነት ለመልካም ነገር አጸናሃለሁ፤ በእውነት በመከራና በጭንቅ ጊዜ ጠላትህ እንዲለምንህ አደርገዋለሁ። 12በውኑ ብረትን፥ የሰሜንን ብረት፥ ናስንም የሚሰብር አለን?
13“በመላ ግዛቶችህ ውስጥ ስላለ ኃጢአትህ ሁሉ ባለጠግነትህንና መዝገብህን ለብዝበዛ በከንቱ አሳልፌ እሰጣለሁ። 14የምታቃጥላችሁ እሳት ከቁጣዬ ትነድዳለችና ከጠላቶችህ ጋር ወደማታውቀው ምድር አሻግርሃለሁስ።”
15አቤቱ! አንተ ታውቃለህ፤ አስታውሰኝ ጐብኘኝም፥ የሚያሳድዱኝንም ተበቀልልኝ፤ ቁጣህንም ከማዘግየትህ የተነሣ እንዳታጠፋኝ፤ ስለ አንተ ስድብን እንደ ታገሥሁ እወቅ። 16ቃላትህ ተገኝተዋል እኔም በልቼአቸዋለሁ፤ አቤቱ! የሠራዊት አምላክ ጌታ ሆይ! በስምህ ተጠርቻለሁና ቃላትህ ሐሤትና የልብ ደስታ ሆኑኝ። 17በዋዘኞች ጉባኤ አልተቀመጥኩም አልተደሰትኩምም፤ ቁጣን ሞልተህብኛልና እጅህ በእኔ ላይ ስለ ሆነ ለብቻዬ ተቀመጥሁ። 18ለምን ሕመሜ የማያቋርጥ ሆነ? ቁስሌስ የማይፈወስ ለምን ሆነ? ለምንስ፦ አልሽርም አለ? በውኑ እንደ ሐሰተኛ ምንጭ፥ እንዳልታመነች ውኃ ትሆንብኛለህን?
19ስለዚህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ብትመለስ እመልስሃለሁ በፊቴም ትቆማለህ፤ የከበረውንም ከተዋረደው ብትለይ እንደ አፌ ትሆናለህ፤ እነርሱ ወደ አንተ ይመለሳሉ፥ አንተ ግን ወደ እነርሱ አትመለስም። 20ለዚህም ሕዝብ የተመሸገ የናስ ቅጥር አደርግሃለሁ፤ ይዋጉሃል እኔ ግን ላድንህና ልታደግህ ከአንተ ጋር ነኝና አያሸንፉህም፥ ይላል ጌታ። 21ከክፉ ሰዎችም እጅ እታደግሃለሁ፥ ከጨካኞችም እጅ እቤዥሃለሁ።”

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}