መጽሐፈ ዮዲት 6
6
የአኪዮር ለእስራኤሎች ተላልፎ መስጠት
1ሸንጎውን ከበው የነበሩት ሰዎች ጫጫታቸውን አቋርጠው ዝም ባሉ ጊዜ የአሦር ዋና የጦር አዛዥ ሆሎፎርኒስ በእንግዳ ሕዝቦች እና በሞዓብ ልጆች ሁሉ ፊት አኪዮርን እንዲህ አለው፦ 2አንተ አኪዮር፥ እናንተም የኤፍሬም ቅጥረኞች፥ አምላካቸው ስለሚጠብቃቸው ከእስራኤል ልጆች ጋር አትዋጉ ብላችሁ ዛሬ ትንቢት የምትናገሩን እናንተ ማን ናችሁ? ከናቡከደነፆር በቀር ሌላ አምላክ ማን ነው? እርሱ የጦር ኃይሉን ልኮ ከምድረ ገጽ ያጠፋቸዋል፤ አምላካቸው አያድናቸውም፤ 3እኛ የናቡከደነፆር ባርያዎች እንደ አንድ ሰው እንመታቸዋለን፤ የፈረሰኞቻችንንም ኃይል ሊቋቋሙ አይችሉም። 4እናቃጥላቸዋለን፤ ተራሮቻቸው በደማቸው ይሰክራሉ፥ ሜዳዎቻቸው በአስክሬን ይሞላሉ፤ የእግራቸው ፍለጋ እንኳ ሊቋቋመን አይችልም፤ ፈጽመው ይጠፋሉ፥ የምድር ሁሉ ጌታ የሆነው ናቡከደነፆር ብሏልና፤ እርሱ ተናግሮአልና፤ ንግግሩ በከንቱ አይቀርም። 5አንተም አክዮር አሞናዊ ቅጥረኛ ከዳተኛ ሆነህ ነው ይህን የተናገርኸው፤ ከዛሬ ጀምሮ ከግብጽ የወጣውን ዘር እስክበቀለው ድረስ ፊቴን አታየውም። 6ተመልሼ ስመጣ የወታደሮቼና የአገልጋዮቼ ጦር ጐኖችህን ይወጋል፤ ከቁስለኞቻቸው መሃል ትወድቃለህ፤ 7አሁን ባርያዎቼ ወደ ተራራማው አገር ይወስዱሃል፥ እዚያም በአንድ ከተማ መተላለፊያ ይጥሉሃል። 8ከእነርሱ ጋር እስክትጠፋ ድረስ አትሞትም። 9አልያዝም ብለህ በልብህ ካሰብህ ፊትህ አይውደቅ፤ እኔ ተናግሬአለሁ፥ ከቃሌም የሚወድቅ የለም። 10ከዚህ በኋላ ሆሎፎርኒስ በድንኳኑ ውስጥ ቆመው ለነበሩት ባርያዎቹ አክዮርን ይዘው ወደ ቤቱሊያ እንዲወስዱትና ለእስራኤልም ልጆች አሳልፈው እንዲሰጡት አዘዘቸው። 11ባርያዎቹም ያዙትና ከሰፈሩ ውጭ ወደ ሜዳ ወሰዱት፤ ከሜዳው ወደ ተራራማው አገር ወጡና ከቤቱሊያ በታች ወዳሉት ምንጮች ደረሱ፤ 12የከተማዋ ሰዎች ባዩአቸው ጊዜ መሣሪያቸውን ይዘው ከከተማዋ ወጥተው ወደ ተራራው ጫፍ ወጡ፥ ወንጭፍ የያዙ ሰዎች ድንጋይ እየወረወሩ ወደ ላይ እዳይወጡ ከለከሉአቸው። 13በተራራው ተደብቀው አክዮርን አስረው በተራራው ሥር ጥለውት ወደ ጌታቸው ተመለሱ። 14የእስራኤልም ልጆች ግን ከከተማቸው ወረዱና ወደ እርሱ ሄዱ፤ ፈትተውትም ወደ ቤቱሊያ አመጡት፥ በከተማቸው ገዢዎች ፊት አቀረቡት፤ 15በዚያን ዘመን ገዢዎች የነበሩት ከስምዖን ነገድ የሆነ የሚካ ልጅ ዑዚያ፥ የጐቶኒኤል ልጅ ካብሪስና የመልኪኤል ልጅ ካርሚስ ናቸው። 16የከተማይቱን ሽማግሌዎች ሁሉ ጠሩ፥ ወጣቶቻቸውና ሴቶቻቸው ሁሉ ወደ ጉባኤው መጡ፤ አክዮርን በሕዝቡ መካከል አቆሙና ዑዚያ ስለተደረገው ነገር ጠየቀው። 17አክዮር በሆሎፎርኒስ ጉባኤ ላይ የተባለውን፥ በአሦር ታላላቅ ሰዎች ፊት የተናገረውን ሁሉና ሆሎፎርኒስ በእስራኤለ ቤት ላይ የፎከረውን ሁሉ ነገራቸው። 18በዚህ ጊዜ ሕዝብ ሁሉ ወድቀው ለእግዚአብሔር ሰገዱ፥ እንዲህም ሲሉ ጮኹ፦ 19“የሰማይ አምላክ ጌታ ሆይ፥ ትዕቢታቸውን ተመልከት፥ የወገኖቻችንን ውርደት አይተህ ይቅር በል፤ በዚህች ቀን ለአንተ የተቀደሱትን ፊት ተመልከት።” 20ከዚህ በኋላ አክዮርን አጽናኑት፥ እጅግም አከበሩት። 21ዑዚያ ከጉባኤው ወደ ቤቱ ወሰደውና ለሽማግሌዎች ግብዣ አደረገ፤ በዚያች ሌሊት ሙሉ የእስራኤል አምላክ እንዲረዳቸው ጠሩት።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዮዲት 6: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ