መጽሐፈ ዮዲት 4

4
የአይሁዳውያን ዝግጅት
1በይሁዳ አገር የሚኖሩ እስራኤላውያን የአሦር ንጉሥ የናቡከደነፆር ዋና የጦር አዛዥ ሆሎፎርኒስ በአሕዛብ ላይ የደረገውን ሁሉ፥ መቅደሳቸውን እንዳፈረሰና እነርሱንም ለጥፋት እንደሰጣቸው በሰሙ ጊዜ፥ 2እጅግ እጅግ ፊቱን ፈሩ፤ ስለ ኢየሩሳሌምና ስለ ጌታ አምላካቸው ቤተ መቅደስ ተጨነቁ። 3ምክንያቱም ከምርኮ የመለሱት በቅርቡ ስለሆነና የይሁዳም ሕዝብ የተሰባሰቡት፥ ዕቃዎቹን መሠዊያውንና መቅደሱንም ከረከሰ በኋላ ያነጹት በቅርቡ ስለ ነበረ ነው። 4ስለዚህም ወደ ሰማርያ፥ ወደ ኮና፥ ወደ ቤትሖሮን፥ ወደ ቤልሜይን፥ ወደ ኢያሪኮ፥ ወደ ቾባ፥ ወደ አይሶራና ወደ ሳሌም ሸለቆ ሁሉ ላኩ። 5የተራሮችን ሁሉ ጫፍ ያዙ፥ በተራሮች ላይ ያሉትንም መንደሮች ቅጥር ሰሩ፥ አዝመራቸው ቀደም ብሎ ተሰብስቦ ስለ ነበር ለጦርነት የሚሆን ስንቅን አዘጋጁ። 6በዚያን ዘመን ሊቀ ካህን የነበረው ኢዮአቄም በቤቱሊያና በዶታይም ሜዳ አጠገብ በኤስድራሎን ፊት ለፊት በምትገኘው በቤቶሜስታይም ለሚኖሩ ሰዎች ጻፈ፤ 7ወደ ተራራው የሚወስደውን መተላለፊያ እንዲይዙ ነገራቸው፤ ምክንያቱም ወደ ይሁዳ መግቢያ በዚያ ስለሆነ፥ መተላለፊያውም በጣም ጠባብ ስለሆነና በአንድ ጊዜ ሁለት ሰው ብቻ የሚያስተላልፍ ስለሆነ የሚገቡትን ሰዎች ለመከላከል ቀላል ስለሆነ ነው። 8የእስራኤልም ልጆች ሊቀ ካህኑ ኢዮአቄምና በኢየሩሳሌም የሚቀመጡ የእስራኤል ሽማግሌዎች ጉባኤ እንደ አዘዙአቸው አደረጉ።
የሕዝብ ጸሎት
9የእስራኤልም ሰዎች ወደ እግዚአብሔር በብርቱ እጅግ ጮሁ፥ በብርቱም ነፍሳቸውን ዝቅ አደረጉ። 10#ዮናስ 3፥7፤8፤ አስ. 4፥1-3።እነርሱና ሚስቶቻቸው፥ ልጆቻቸው፥ ከብቶቻቸው፥ በዚያ የሚኖሩ እንግዶች ሁሉ፥ ቅጥረኞችና በብር የተገዙ ሁሉ በወገባቸውን በማቅ ታጠቁ። 11በኢየሩሳሌም የሚኖሩ የእስራኤል ሰዎች ሁሉ፥ ሴቶችና ሕፃናትም በቤተ መቅደሱ ፊት ተደፉ፤ በራሶቻቸውም ላይ አመድ ነሰነሱ፥ በጌታ ፊት ማቃቸውን ዘረጉ። 12መሠዊያውንም ማቅ አለበሱ፤ ልጆቻቸውና ሚስቶቻቸው እንዳይዘረፉ፤ የወረሱአቸው ከተሞቻቸው እንዳይደመሰሱ፤ የተቀደሰው ቦታ በአረመኔዎች እንዳይረክስና እንዳይዋረድ ወደ እግዚአብሔር አጥብቀው ባንድነት አለቀሱ። 13#አስ. 4፥16።ጌታ ድምጻቸውን ሰማ፥ መከራቸውንም አየ፤ ሕዝቡ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ሁሉን በሚችል በጌታ መቅደስ ፊት ለብዙ ቀኖች ጾሙ። 14#ኢዩ. 2፥17።ሊቀ ካህኑ ኢዮአቄምና በጌታ ፊት የሚቆሙት ካህናት ሁሉና ጌታን የሚያገለግሉ ሁሉ በወገባቸው ማቅ ታጥቀው የሕዝቡን የሚቃጠል መሥዋዕት፥ የዘወትር መሥዋዕት፥ ስእለትና በፈቃድ የሚሰጠውንም ሥጦታ አቀረቡ። 15ጥምጣማቸው ላይ አመድ ነስንሰው፥ መላውን የእስራኤል ቤት በመልካም እንዲጎበኝ በሙሉ ኃይላቸው ወደ ጌታ ጮኹ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ