መጽሐፈ ዮዲት 1

1
1 የሆሎፎርኒስ ዘመቻ
ናቡከደነፆርና አርፋስክድ
1በታላቂቱ ከተማ በነነዌ በአሦራውያን ላይ የገዛው ናቡከደነፆር ከነገሠ ዐሥራ ሁለተኛው ዓመት ነበር፤ በዚያን ጊዜ አርፋክስድ በኤቅባጥና ባሉ በሜዶናውያን ላይ ነግሦ ነበር። 2በኤቅባጥና ከተማ ዙሪያ ስፋታቸው ሦስት ክንድ፥ ቁመታቸው ስድስት ክንድ የሆኑ በተጠረበ ድንጋይ ቅጥሮችን ገነባ። የቅጥሮቹ ቁመት ሰባ ክንድ፥ ስፋቱ ሃምሳ ክንድ አድርጎ ሠራ። 3በየበሮች ቁመታቸው መቶ ክንድ፥ የመሠረታቸው ስፋት ስለሳ ክንድ የሆኑ ግንቦች አቁሞ ነበር። 4የበራፎቹ ቁመት ወደ ላይ ሰባ ክንድ ጐናቸው አርባ ክንድ ሆኖ የእግረኛ ጦር ወታደሮች በሰልፍ እንዲወጡባቸው ሆነው የተሠሩ ነበሩ። 5በእነዚያ ቀኖች ንጉሥ ናቡከደነፆር በሰፊ ሜዳ በንጉሥ አርፋክስድ ላይ ጦርነት ከፈተ፥ ያም በራጋው አውራጃ ያለ ሜዳ ነው። 6በአምባው የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ፥ በኤፈራጥስ፥ በጤግራን፥ በሄዳስጴን ያሉ ሁሉ፥ በኤለሜዖን ንጉሥ በአርዮክ ግዛት ያሉ ሁሉ ከናቡከደነፆር ጋር ወገኑ፥ ብዙ ሕዝቦችም የካሉድን ልጆች ለመውጋት ተሰበሰቡ። 7ከዚህ በኋላ የአሦር ንጉሥ ናቡከደነፆር በፋርስ ለሚኖሩ ሁሉ፥ በምዕራብ ለሚኖሩ ሁሉ፥ በኪልቅያና በደማስቆ፥ በሊባኖስና በአንቲሊባኖስ ለሚኖሩ ሁሉ፥ በባሕር ጠረፍ ለሚገኙ ሁሉ ላከ፥ 8በቀርሜሎስና በገለዓድ ሕዝቦች መካከል ላሉ፥ በላይኛው ገሊላና በሰፊው በኤስድራሎን ሜዳ ለሚኖሩ ሁሉ፥ 9በሰማርያና በከተሞችዋ ላሉ ሁሉ፥ በዮርዳኖስ ማዶ እስከ ኢየሩሳሌም፥ ባታኒ፥ ኬሎስ፥ ቃዴስ፥ የግብጽ ወንዝ፥ ታፍናስ፥ ራምሴና ጌሴም ምድር ሁሉ፥ 10እስከ ጣኒስና ሜምፊስ በላይ፥ በግብጽ እስከ ኢትዮጵያ ድንበር ድረስ ለሚኖሩ ሁሉ ላከ። 11ነገር ግን በምድሪቱ የሚኖሩ ሁሉ የአሦርን ንጉሥ የናቡከደነፆርን ቃል ንቀው ከእሱ ጋር በጦርነት ላይ ለመሰለፍ እንቢ አሉ፤ አልፈሩትምና፥ እንደ አንድ ሰው ቆጥረዉታልና፤ መልክተኞቹንም ባዶ እጃቸውንና አዋርደው ከፊታቸው መለሱአቸው። 12ናቡከደነዖር በምድሪቱ ሁሉ ላይ እጅግ ተቆጣ፥ የኪልቅያን፥ የደማስቆን፥ የሶርያን አገሮች እንደሚበቀል፥ በሞዓብን ምድር የሚኖሩትን ሁሉ፥ የአሞንን ልጆች፥ ይሁዳን በሙሉ፥ እስከ ሁለት ባሕሮች ጠረፍ ድረስ በግብጽ የሚኖሩትንም ሁሉ በሰይፍ እንደሚገድል በዙፋኑና በመንግሥቱ ማለ።
አርፋክስድ እንደ ተሸነፈ
13በዓሥራ ሰባተኛው ዓመት ሠራዊቱን በንጉሥ አርፋክስድ ላይ አሰለፈ፥ በጦርነቱም አሸነፈ፥ የአርፋክስድን ሠራዊቱን ሁሉ፥ ፈረሰኞቹንና ሠረገላዎቹን ገለበጠ። 14በከተሞቹም ላይ ጌታ ሆነ፥ እስከ ኤቅባጥናም ደረሰ፥ ግንቦቹን ያዘ፥ አደባባዮቸን በረበረ፥ ክብርዋንም በውርደት ቀየረው። 15አርፋክስድንም በራግው ተራሮች ላይ ያዘውና በጦር ወጋው፥ እስከዚህችም ቀን ድረስ አጠፋው። 16ከዚህ በኋላ ከመላ ሠራዊቱና ከብዙ ጦረኞቹ ጋር ተመለሰ፤ በዚያም እርሱና ሠራዊቱ ሁሉ እየበሉና እየጠጡ መቶ ሃያ ቀን ተቀመጡ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ