የያዕቆብ መልእክት 5:7-20

የያዕቆብ መልእክት 5:7-20 መቅካእኤ

እንግዲህ ወንድሞች ሆይ! ጌታ እስከሚመጣ ድረስ ታገሡ። እነሆ ገበሬ መሬቱ መልካምን ፍሬ እስከሚሰጥ ድረስ እንዴት እንደሚታገሥ፥ የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እንዴት እንደሚጠባበቅ አስተውሉ። እናንተም እንዲሁ ታገሡ፤ ልባችሁንም አጽኑ፤ ምክንያቱም የጌታ መምጫ ተቃርቦአልና። ወንድሞች ሆይ! እንዳይፈረድባችሁ፥ እርስ በርሳችሁ አታጉረምርሙ፤ እነሆ ፈራጁ በበር ላይ ቆሞአል። ወንድሞች ሆይ! በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያት የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ አድርጋችሁ ተመልከቱ። በትዕግሥት የጸኑትን የተባረኩ አድርገን እንደምንቈጥር ታውቃላችሁ፤ ኢዮብ እንዴት ታግሦ እንደ ጸና ሰምታችኋል፤ ጌታም በመጨረሻ ያደረገለትን አይታችኋል። ጌታ እጅግ ርኅሩኅና መሓሪ ነው። ከሁሉም በላይ ወንድሞቼ ሆይ! በሰማይ ወይም በምድር ወይም በማናቸውም ነገር ቢሆን አትማሉ፤ ነገር ግን ከፍርድ በታች እንዳትወድቁ፥ ነገራችሁ “አዎ” ቢሆን አዎ ይሁን፤ “አይደለም” ቢሆን አይደለም ይሁን። ከእናንተ መካከል በመከራ ውስጥ ያለ አለ? እርሱ ይጸልይ፤ የተደሰተ አለ? የምስጋና መዝሙር ይዘምር። ከእናንተ መካከል የታመመ ሰው አለ? የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን ይጥራ፤ እነርሱም በጌታ ስም ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። በእምነት የቀረበ ጸሎት የታመመውን ሰው ይፈውሰዋል፤ ጌታም ያስነሣዋል፤ ኃጢአትም ሠርቶ ከሆነ፥ ይቅር ይባላል። ስለዚህ ኀጢአታችሁን እርስ በርሳችሁ ተናዘዙ፤ ትፈወሱም ዘንድ አንዱ ለሌላው ይጸልይ። የጻድቅ ሰው ጸሎት ኃይል አለው፤ ታላቅ ነገርም ያደርጋል። ኤልያስ እንደ እኛ ሰው ነበረ፤ ዝናብ እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፤ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ተኩል ዝናብ አልዘነበም። እንደገና በጸለየም ጊዜ ሰማይ ዝናብ ሰጠ፤ ምድርም ፍሬን ሰጠች። ወንድሞቼ ሆይ! ከእናንተ አንዱ ከእውነት ቢስትና ሌላው ቢመልሰው፥ ይህን ይወቅ፤ ኀጢአተኛን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልስ ሰው ነፍሱን ከሞት ያድንለታል፤ ብዙ ኃጢአቱንም ይቅርታ ያስገኝለታል።