ወደ ዕብራውያን 9:16-28

ወደ ዕብራውያን 9:16-28 መቅካእኤ

ኑዛዜ ካለ የተናዛዡን ሞት ማርዳት የግድ ነውና፥ ሰው ሲሞት ኑዛዜው ይጸናል። ተናዛዡ በሕይወት ካለ ግን ከቶ አይጠቅምም። ስለዚህም ፊተኛው ኪዳን እንኳን ያለ ደም አልተመረቀም። እያንዳንዱን የሕግ ትእዛዝ በሙሴ ለሕዝቡ ከተነገረ በኋላ የጥጆችን ደም ከውሃ፥ ከቀይ የበግ ጠጒርና ከሂሶጵ ጋር ወስዶ፥ በመጽሐፉና በሕዝቡ ላይ ረጨው፤ “እንድትጠብቁት እግዚአብሔር ያዘዛችሁ የኪዳኑ ደም ይህ ነው።” አላቸው። በተመሳሳይ በድንኳኒቱና በማገልገያው ዕቃ ሁሉ ደምን ረጭቷል። እንደ ሕጉም ከጥቂቶች በቀር ነገር ሁሉ በደም ይነጻል፤ ደምም ሳይፈስ ስርየት የለም። እንግዲህ የሰማያዊው ነገሮች ምሳሌ የሆኑት እነዚህ ነገሮች በዚህ ሥርዓት ሊነጹ ግድ ነበር፤ ነገር ግን ሰማያዊ ነገሮች ራሳቸው ከእርሱ ይልቅ በሚበልጥ መሥዋዕት ይነጻሉ። ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሠራች፥ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደምትሆን ቅድስት አልገባም፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ለመታየት ወደ እርሷ ወደ ሰማይ ገባ። ሊቀ ካህናትም በየዓመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት ደጋግሞ እንደሚገባ፥ ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም፤ እንዲህ ቢሆን ኖሮ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር፤ አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል። ለሰዎችም አንድ ጊዜ ለመሞት ከዚያም ለፍርድ መቅረብ ተመድቦባቸዋል። እንዲሁም ክርስቶስ፥ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ተሰውቷል። ለሁለተኛ ጊዜ ሲታይ ሊያድናቸው ለሚጠባበቁት ኃጢአትን ለመሸከም ሳይሆን መዳንን ለማምጣት ነው።