ይስሐቅም በዚያች ምድር ዘርን ዘራ፥ በዚያች ዓመትም መቶ እጥፍ አገኘ፥ እግዚአብሔርም ባረከው። ባለ ጠጋ ሰውም ሆነ፥ እጅግ እስኪበልጥ ድረስም እየጨመረ ይበዛ ነበር፥ በግና ላም ከብትም ሎሌዎችም እጅግ በዙለት፥ የፍልስጥኤም ሰዎች ቀኑበት። በአባቱ በአብርሃም ዘመን የአባቱ ሎሌዎች የማሱአቸውን ጉድጓዶች ሁሉ የፍልስጥኤም ሰዎች ደፈኑአቸው፥ አፈርንም ሞሉባቸው። አቢሜሌክም ይስሐቅን፦ “ከእኛ ተለይተህ ሂድ፥ ከእኛ ይልቅ እጅግ በርትተሃልና” አለው። ይስሐቅም ከዚያ ሄደ፥ በጌራራም ሸለቆ ተቀመጠ። ይስሐቅም በአባቱ በአብርሃም ዘመን ቈፍረዋቸው የነበሩትን የውኃ ጉድጓዶች ደግሞ አስቈፈረ፥ አብርሃም ከሞተ በኋላ የፍልስጥኤም ሰዎች ደፍነዋቸው ነበሩና፥ አባቱም ይጠራቸው በነበረው ስም ጠራቸው። የይስሐቅ ሎሌዎችም በሸለቆው ውስጥ ቈፈሩ፥ በዚያም የሚመነጭ የውኃ ጉድጓድ አገኙ። የጌራራ አገር እረኞች ከይስሐቅ እረኞች ጋር፦ “ውኃው የእኛ ነው” ሲሉ ተከራከሩ፥ የዚያችንም ጉድጓድ ስም “ኤሴቅ” ብሎ ጠራት፥ ለእርሷ ሲሉ ተጣልተዋልና። ሌላ ጉድጓድም ማሱ፥ ስለ እርሷም ደግሞ ተጣሉ፥ ስምዋንም “ስጥና” ብሎ ጠራት። ከዚያም እልፍ ብሎ ሌላ ጉድጓድ አስቈፈረ፥ ስለ እርሷም አልተጣሉም፥ ስምዋንም “ርኆቦት” ብሎ ጠራት እንዲህ ሲል፦ “አሁን እግዚአብሔር አሰፋልን፥ በምድርም እንበዛለን።” ከዚያም ወደ ቤርሳቤህ ወጣ። በዚያችም ሌሊት ጌታ ተገለጠለት፥ እንዲህም አለው፦ “እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ ነኝ፥ አትፍራ፥ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና፥ እባርክሃለሁ፥ ስለ ባርያዬ ስለ አብርሃም ዘርህን አበዛለሁ።” በዚያም መሠዊያን ሠራ የጌታንም ስም ጠራ፥ በዚያም ድንኳን ተከለ፥ የይስሐቅም አገልጋዮች በዚያ ጉድጓድ ማሱ። አቢሜሌክና የሙሽራው ወዳጅ አኮዘት የሠራዊቱም አለቃ ፊኮል ከጌራራ ወደ እርሱ ሄዱ። ይስሐቅም፦ “ለምን ወደ እኔ መጣችሁ? እናንተ ጠልታችሁኛል፥ ከእናንተም ለይታችሁ አሳድዳችሁኛል” አላቸው። እነርሱም፤ “ጌታ ከአንተ ጋር መሆኑን በግልጥ አየን፤ ስለዚህ በእኛና በአንተ መካከል መሐላ ይኑር፤ ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን እንጋባ፥ እኛ አንተን እንዳልነካንህ፥ በጎነትንም ብቻ እንዳሳየንህ፥ በሰላምም እንደ ሰደድንህ፥ አንተም ክፉ እንዳትሠራብን፥ አንተ አሁንም ከጌታ ዘንድ የተባረክህ ነህ።” ይስሐቅም ማዕድ አቀረበላቸው፥ በሉም ጠጡም። ማልደውም ተነሡ፥ እርስ በርሳቸውም ተማማሉ፥ ይስሐቅም አሰናበታቸው፥ ከእርሱም ወጥተው በሰላም ሄዱ። በዚያም ቀን የይስሐቅ አገልጋዮች መጡ፥ ስለ ቈፈሩአትም ጉድጓድ፦ “ውኃ አገኘን ብለው ነገሩት።” ስምዋንም “ሳቤህ” ብሎ ጠራት፥ ስለዚህም የከተማይቱ ስም እስከ ዛሬ ድረስ ቤርሳቤህ ነው። ዔሳውም አርባ ዓመት ሲሆነው የሒታውያዊ የብኤሪን ልጅ ዮዲትን፥ የሒታውያዊ የኤሎንን ልጅ ቤሴሞትንም ሚስቶች አድርጎ አገባ፥ እነርሱም የይስሐቅንና የርብቃን ልብ ያሳዝኑ ነበር።
ኦሪት ዘፍጥረት 26 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 26:12-35
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች