ኦሪት ዘፍጥረት 18:4-15
ኦሪት ዘፍጥረት 18:4-15 መቅካእኤ
ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ፥ እግራችሁን ታጠቡ፥ ከዚህችም ዛፍ በታች ዕረፉ፥ ቁራሽ እንጀራም ላምጣላችሁ፥ ልባችሁንም ደግፋ ከዚያም በኋላ ትሄዳላችሁ፥ ስለዚህ ወደ ባርያችሁ መጥታችኋልና።” እነርሱም፦ “እንዳልህ አድርግ” አሉት። አብርሃምም ወደ ድንኳን ወደ ሣራ ዘንድ ፈጥኖ ገባና፦ “ሦስት መስፈሪያ የተሰለቀ ዱቄት ፈጥነሽ አዘጋጂ፥ ለውሺውም፥ እንጎቻም አድርጊ” አላት። አብርሃምም ወደ ላሞቹ ሮጠ፥ እጅግ የሰባም ታናሽ ጥጃ ያዘና ለብላቴናው ሰጠው፥ ያዘጋጅም ዘንድ ተቻኰለ። እርጎና ወተት፥ ያዘጋጀውንም ጥጃ አመጣ፥ በፊታቸውም አቀረበው፥ እርሱም ከዛፉ በታች በፊታቸው ቆሞ ነበር፥ እነርሱም በሉ። እነርሱም፦ “ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት?” አሉት። እርሱም፦ “በድንኳኑ ውስጥ ናት” አላቸው። እርሱም፦ “የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ፥ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች” አለ። ሣራም በድንኳን ደጃፍ በስተ ኋላው ሳለች ይህንን ሰማች። አብርሃምና ሣራም በዕድሜአቸው ሸምግለው ፈጽመው አርጅተው ነበር፥ በሴቶች የሚሆነውም ልማድ ከሣራ ተቋርጦ ነበር። ሣራም በልብዋ እንዲህ ስትል ሳቀች፦ “ካረጀሁ በኋላ በውኑ ፍትወት ይሆንልኛልን? ጌታዬም ፈጽሞ ሸምግሎአል።” እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፦ “ካረጀሁ በኋላ በውኑ እወልዳለሁን? ስትል ሣራ ለምን ሳቀች? በውኑ ለጌታ የሚሳነው ነገር አለን? የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ እመለሳለሁ፥ ሣራም ልጅን ታገኛለች።” ሣራም ስለ ፈራች፦ “አልሳቅሁም” ስትል ካደች። እርሱም፦ “አይደለም፥ ሳቅሽ እንጂ” አላት።

