ኦሪት ዘፍጥረት 14:1-16

ኦሪት ዘፍጥረት 14:1-16 መቅካእኤ

በሰናዖር ንጉሥ በአምራፌል፥ በእላሳር ንጉሥ በአርዮክ፥ በኤላም ንጉሥ በኮሎዶጎምር፥ በአሕዛብ ንጉሥ በቲድዓል ዘመን እንዲህ ሆነ ከሰዶም ንጉሥ ከባላ፥ ከገሞራ ንጉሥ ከብርሳ፥ ከአዳማ ንጉሥ ከሰነአብ፥ ከሰቦይም ንጉሥ ከሰሜበር፥ ዞዓር ከተባለች ከቤላ ንጉሥም ጋር ሰልፍ አደረጉ። እነዚህ ሁሉ በሲዲም ሸለቆ ተሰብስበው ተባበሩ፥ ይኸውም የጨው ባሕር ነው። ዐሥራ ሁለት ዓመት ለኮሎዶጎምር ተገዝተው ነበር፥ በዓሥራ ሦስተኛውም ዓመት ዐመፁ። በዓሥራ አራተኛውም ዓመት ኮሎዶጎምርና ከእርሱ ጋር የነበሩት ነገሥታት መጡ፥ ራፋይምን በአስጣሮት ቃርናይም፥ ዙዚምንም በሃም፥ ኤሚምንም በሴዊ ቂርያታይም መቱ፥ የሖር ሰዎችንም በሴይር ተራራቸው በበረሀ አጠገብ እስካለች እስከ ኤል ፋራን ድረስ መቱ። ተመልሰውም ቃዴስ ወደተባለች ወደ ዓይንሚስፓጥ መጡ፥ የአማሌቅን አገር ሁሉና ደግሞ በሐሴቦን ታማር የነበረውን አሞራውያንን መቱ። የሰዶም ንጉሥና የገሞራ ንጉሥ፥ የአዳማ ንጉሥና የሰቦይም ንጉሥ፥ ዞዓር የተባለች የቤላ ንጉሥም ወጡ፥ እነዚህ ሁሉ በሲዲም ሸለቆ በእነርሱ ላይ ለሰልፍ ወጡ፥ የኤላምን ንጉሥ ኮሎዶጎምርን፥ የአሕዛብን ንጉሥ ቲድዓልን፥ የሰናዖርን ንጉሥ አምራፌልን፥ የእላሳርን ንጉሥ አርዮክን ለመውጋት አምስቱ ነገሥታት በእነዚህ በአራቱ ላይ ወጡ። በሲዲም ሸለቆ ግን የዝፍት ጉድጓዶች ነበሩበት። የሰዶም ንጉሥ የገሞራ ንጉሥም ሸሹና ወደዚያ ወደቁ፥ የቀሩትም ወደ ተራራ። ሸሹ። የሰዶምንና የገሞራን ከብት ሁሉ መብላቸውንም ሁሉ ወስደው ሄዱ። በሰዶም ይኖር የነበረውን የአብራምን የወንድም ልጅ ሎጥን ደግሞ ከብቱንም ወስደው ሄዱ። አንድ የሸሸ ሰውም መጣ፥ ለዕብራዊው ለአብራምም ነገረው፥ እርሱም የኤስኮል ወንድምና የአውናን ወንድም በሆነ በአሞራዊ መምሬ የባሉጥ ዛፎች አጠገብ ይኖር ነበር፥ እነዚያም ከአብራም ጋር ቃል ኪዳን ገብተው ነበር። አብራምም ወንድሙ እንደ ተማረከ በሰማ ጊዜ በቤቱ የተወለዱትን ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ብላቴኖቹን አሰለፈ፥ ፍለጋቸውንም ተከትሎ እስከ ዳን ድረስ ሄደ። አብራምም ጠላቶቹን ለማጥቃት አገልጋዮቹን በቡድን ከፋፍሎ በሌሊት እርሱ ከባርያዎቹ ጋር ወረደባቸው፥ መታቸውም፥ በደማስቆ ግራ እስካለችውም እስከ ሖባ ድረስ አሳደዳቸው። ከብቱንም ሁሉ አስመለሰ፥ ደግሞም ወንድሙን ሎጥንና ከብቶቹን ሴቶችንና ሕዝቡን ደግሞ መለሰ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}