ከዚያ በኋላ በወንዝ ማዶ ያለ አካባቢ ገዢ ታትናይ፥ ሽታርቦዝናይና ተባባሪዎቻቸው ንጉሡ ዳርዮስ እንደ ላከው ቃል፥ እንዲሁ ተግተው አደረጉ። የአይሁድም ሽማግሌዎች በነቢዩ ሐጌና በዒዶ ልጅ በዘካርያስ ትንቢት እየተበረታቱ ሠሩ ተከናወነላቸውም። በእስራኤል አምላክ ትእዛዝ፥ እንደ ቂሮስ ትእዛዝ እንደ ዳርዮስ እንደ አርጤክስስ የፋርስ ንጉሥ ትእዛዝ ሠርተው ፈጸሙ። ይህም ቤት በንጉሡ በዳርዮስ መንግሥት በስድስተኛው ዓመት አዳር በሚባል ወር በሦስተኛው ቀን ተፈጸመ። የእስራኤል ልጆች፥ ካህናትና ሌዋውያን የቀሩትም ምርኮኞች፥ የዚህን የእግዚአብሔርን ቤት ምረቃ በደስታ አከበሩ። ለዚህ የእግዚአብሔር ቤት ምረቃ አንድ መቶ ወይፈኖች፥ ሁለት መቶ አውራ በጎች፥ አራት መቶ የበግ ጠቦቶችን፥ ስለ ኃጢአትም መሥዋዕት እንደ እስራኤል ነገዶች ቍጥር ለእስራኤል ሁሉ ዐሥራ ሁለት አውራ ፍየሎች አቀረቡ። በሙሴም መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት በኢየሩሳሌም ባለው በእግዚአብሔር አገልግሎት ላይ ካህናቱን በየማዕረጋቸው ሌዋውያኑንም በየክፍላቸው መደቡአቸው። ምርኮኞቹም በመጀመሪያው ወር በዓሥራ አራተኛው ቀን ፋሲካውን አከበሩ። ካህናቱና ሌዋውያኑ እንደ አንድ ሰው ሆነው እራሳቸውን አነጹ፥ ሁሉም ንጹሐን ነበሩ፥ ከምርኮ ለተመለሱ ሕዝቦች ሁሉ፥ ለወንድሞቻቸው ለካህናቱና ለራሳቸው ፋሲካውን አረዱ። ከምርኮ የተመለሱት የእስራኤል ልጆች፥ የእስራኤልን አምላክ ጌታን ለመፈለግ ራሳቸውን ከምድር አሕዛብ ርኩሰት ለይተው ወደ እነርሱ መጥተው የነበሩት ሁሉ በሉት። ጌታ ደስ አሰኝቶአቸዋልና፥ የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ቤትም ለመሥራት እጃቸውን እንዲያጸኑ የአሦርን ንጉሥ ልብ ወደ እነርሱ መልሶአልና የቂጣውን በዓል ሰባት ቀን በደስታ አከበሩ።
መጽሐፈ ዕዝራ 6 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ዕዝራ 6:13-22
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች