እንዲህም ሆነ በሰባተኛው ዓመት፥ በአምስተኛው ወር፥ ከወሩም በአሥረኛው ቀን፥ ከእስራኤል ሽማግሌዎች ሰዎች ጌታን ሊጠይቁ መጡ፥ በፊቴም ተቀመጡ። የጌታም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤልን ሽማግሌዎች ተናገራቸው፥ እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እናንተ እኔን ልትጠይቁ መጣችሁን? እኔ ሕያው ነኝ፥ ለእናንተ አልጠየቅም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ትፈርድባቸዋለህን? የሰው ልጅ ሆይ፥ ትፈርድባቸዋለህን? የአባቶቻቸውን ርኩሰት አስታውቃቸው፤ እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እስራኤልን በመረጥሁበት ቀን፥ ለያዕቆብ ቤት ዘር ማልሁላቸው፥ በግብጽም ምድር ራሴን ገለጥሁላቸው፦ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ ብዬ ማልሁላቸው። በዚያ ቀን ከግብጽ ምድር ወዳዘጋጀሁላችሁ፥ ወተትና ማር ወደምታፈስሰው፥ የምድርም ሁሉ ጌጥ ወደምትሆን ምድር አወጣቸው ዘንድ ማልሁላቸው። እኔም፦ ከእናንተ እያንዳንዱ የዓይኑን ርኩሰት ይጣል፥ በግብጽም ጣዖታት አትርከሱ፤ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ አልኋቸው። እነርሱ ግን ዐመፁብኝ ይሰሙኝም ዘንድ አልወደዱም፥ ሁሉም እያንዳንዱ የዓይኑን ርኩሰት አልጣለም የግብጽንም ጣዖታት አልተወም፤ በዚህም ጊዜ፦ በግብጽ ምድር መካከል ቁጣዬን እፈጽምባቸው ዘንድ መዓቴን አፈስስባቸዋለሁ አልሁ። ነገር ግን በመካከላቸው ባሉ ከግብጽም ምድር አወጣቸው ዘንድ በፊታቸው በተገለጥሁላቸው በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ብዬ ስለ ስሜ ሠራሁ። ከግብጽም ምድር አወጣኋቸው ወደ ምድረ በዳም አመጣኋቸው። ሰው ቢያደርገው ኖሮ በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዓቴንም ሰጠኋቸው፥ ፍርዴንም አስታወቅኋቸው። የምቀድሳቸውም እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቁ ዘንድ፥ በእኔና በእነርሱ መካከል ምልክት ይሆኑ ዘንድ ሰንበታቴን ሰጠኋቸው። ነገር ግን የእስራኤል ቤት በምድረ በዳ ዐመፁብኝ፤ ሰው ቢያደርገው ኖሮ በሕይወት የሚኖርበትንም ፍርዴን ጣሱ፥ በትእዛዜም አልሄዱም፥ ሰንበታቴንም ፈጽመው አረከሱ። በዚህም ጊዜ፦ አጠፋቸው ዘንድ ቁጣዬን በምድረ በዳ አፈስስባቸዋለሁ አልሁ። ነገር ግን በፊታቸው ባወጣኋቸው በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ብዬ ስለ ስሜ ሠራሁ። ወተትና ማርም ወደምታፈስሰው የምድር ሁሉ ጌጥ ወደምትሆን ወደ ሰጠኋቸው ምድር አላመጣቸውም ብዬ በምድረ በዳ ማልሁባቸው። ልባቸው ጣዖቶቻቸውን ተከትሎአልና፥ ፍርዴንም ጥሰዋልና፥ በሥርዓቴም አልሄዱምና፥ ሰንበታቴንም አርክሰዋልና። ነገር ግን ዓይኔ ራራችላቸው እኔም አላጠፋኋቸውም፥ በምድረ በዳም ፈጽሜ አልፈጀኋቸውም። ለልጆቻቸውም በምድረ በዳ እንዲህ አልኋቸው፦ በአባቶቻችሁ ሥርዓት አትሂዱ ወጋቸውንም አትጠብቁ በጣዖቶቻቸውም አትርከሱ። እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ፤ በትእዛዜ ሂዱ ፍርዴንም ጠብቁ አድርጓትም። ሰንበታቴንም ቀድሱ፤ እኔም ጌታ አምላካችሁ እንደሆንሁ እንድታውቁ በእኔና በእናንተ መካከል ምልክት ይሆናሉ። ልጆች ግን ዐመፁብኝ፥ ሰው ቢያደርገው ኖሮ በሕይወት የሚኖርባትን ፍርዴን ጠብቀው አላደረጓትም በሥርዓቴም አልሄዱም፥ ሰንበታቴንም አረከሱ፤ በዚህም ጊዜ፦ መዓቴን አፈስስባቸዋለሁ ቁጣዬንም በምድረ በዳ እፈጽምባቸዋለሁ አልሁ። ነገር ግን እጄን መለስሁ፥ በፊታቸውም ባወጣኋቸው በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ብዬ ስለ ስሜ ሠራሁ። ደግሞም ወደ አሕዛብ እበትናቸው ዘንድ፥ በአገሮችም እበትናቸው ዘንድ በምድረ በዳ ማልሁባቸው፤ ፍርዴን አላደረጉምና፤ ሥርዓቴንም ጥሰዋልና፤ ሰንበታቴንም አርክሰዋልና፤ ዓይናቸውም የአባቶቻቸውን ጣዖታቶች ተከትለዋልና። ደግሞም መልካም ያልሆነውን ሥርዓት በሕይወት የማይኖሩበትንም ፍርድ ሰጠኋቸው። እኔም ጌታ እንደሆንሁ እንዲያውቁ አጠፋቸው ዘንድ፥ ማኅፀን የሚከፍተውን ሁሉ በእሳት ባሳለፉ ጊዜ፥ በመባቸው አረከስኋቸው። ስለዚህ፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ቤት ተናገር እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዚህም ደግሞ አባቶቻችሁ ባደረጉት ዓመጽ አስቆጡኝ። እሰጣቸውም ዘንድ ወደ ማልሁላቸው ምድር ባገባኋቸው ጊዜ፥ ከፍ ያለውን ኮረብታ ሁሉ ቅጠልማውንም ዛፍ ሁሉ አዩ፥ በዚያም መሥዋዕታቸውን ሠዉ በዚያም የሚያስቆጣኝን ቁርባናቸውን አቀረቡ በዚያም ደግሞ ጣፋጩን ሽታቸውን አደረጉ በዚያም የመጠጥ ቁርባናቸውን አፈሰሱ። እኔም፦ እናንተ ወደ እርሱ የምትሄዱበት ከፍታ ምንድነው? አልኋቸው። እስከ ዛሬም ድረስ ስሙ ባማ ተብሎ ተጠርቶአል። ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እንደ አባቶቻችሁ ልማድ ትረክሳላችሁን? ርኩሰታቸውንም ተከትላችሁ ታመነዝራላችሁን? ቁርባናችሁን ባቀረባችሁ ጊዜ፥ ልጆቻችሁንም በእሳት ባሳለፋችሁ ጊዜ፥ እስከ ዛሬ ድረስ በጣዖቶቻችሁ ትረክሳላችሁን የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ከእናንተስ ዘንድ እጠየቃለሁን? እኔ ሕያው ነኛና ከእናንተ ዘንድ አልጠየቅም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ለእናንተም፦ እንደ አሕዛብና እንደ ምድር ወገኖች እንሆናለን፥ እንጨትና ድንጋይም እናመልካለን የሚል ከልባችሁ የወጣ አሳብ አይፈጸምላችሁም። እኔ ሕያው ነኝና በበረታች እጅና በተዘረጋች ክንድ በፈሰሰችም መዓት እነግሥባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ከአሕዛብም ዘንድ አወጣችኋለሁ ከተበተናችሁባትም አገር ሁሉ በበረታች እጅና በተዘረጋች ክንድ በፈሰሰችም መዓት እሰበስባችኋለሁ። ወደ አሕዛብም ምድረ በዳ አመጣችኋለሁ በዚያም ፊት ለፊት ከእናንተ ጋር እፋረዳለሁ። በግብጽ ምድረ በዳ ከአባቶቻችሁ ጋር እንደ ተፋረድሁ እንዲሁ ከእናንተ ጋር እፋረዳለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ከበትርም በታች አሳልፋችኋለሁ ወደ ቃል ኪዳንም እስራት አገባችኋለሁ፤ ከእናንተም ዘንድ ዓመፀኞችንና የበደሉኝን እለያለሁ። ከኖሩባትም ምድር አወጣቸዋለሁ፥ ወደ እስራኤል ምድር ግን አይገቡም፥ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።
ትንቢተ ሕዝቅኤል 20 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ሕዝቅኤል 20:1-38
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች