እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም የሚደረገውን ግፍ ሁሉ አየሁ፥ እነሆም፥ የተገፉት ሰዎች እንባ፥ የሚያጽናናቸውም አልነበረም፥ በሚገፉአቸውም እጅ ኃይል ነበረ፥ እነርሱን ግን የሚያጽናናቸው አልነበረም። እኔም እስከ ዛሬ በሕይወት ካሉት ይልቅ በቀድሞ ዘመን የሞቱትን አመሰገንሁ፥ ከእነዚህም ከሁለቱ ይልቅ ገና ያልተወለደው ከፀሐይም በታች የሚደረገውን ግፍ ያላየው ይሻላል። ደግሞም የሰውን ድካምና የብልሃት ሥራውን ሁሉ ተመለከትሁ፥ በባልንጀራም ዘንድ ቅንዓት እንደሚያስነሣ አየሁ፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። አላዋቂ እጆቹን አጥፎ ይቀመጣል፥ የገዛ ሥጋውንም ይበላል። በድካምና ነፋስን በመከተል ከሚገኝ ሁለት እፍኝ ይልቅ፥ በእርጋታ የሚገኝ አንድ እፍኝ ይሻላል። እንደገና፥ ከፀሐይ በታችም ከንቱ ነገር አየሁ። አንድ ሰው ብቻውን ይኖራል፥ ማንም አብሮት የለም፥ ልጅም ሆነ ወንድም የለውም፥ ለድካሙም መጨረሻ የለውም፥ ዐይኖቹም ሳይቀሩ ሀብትን አይጠግቡም። እንግዲህ ለማን እደክማለሁ፥ ሰውነቴንስ መልካሙን ነገር ለምን እነፍጋታለሁ? ይላል። ይህም ደግሞ ከንቱ ነገር ክፉም ጥረት ነው። ድካማቸው መልካም ዋጋ አለውና አንድ ብቻ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል። ቢወድቁ አንዱ ሁለተኛውን ያነሣዋልና፥ አንዱ ብቻውን ሆኖ በወደቀ ጊዜ ግን የሚያነሣው ሁለተኛ የለውምና ወዮለት። ሁለቱም በአንድነት ቢተኙ ይሞቃቸዋል፥ አንድ ብቻውን ግን እንዴት ይሞቀዋል? አንዱም አንድን ሰው ቢያሸንፍ፥ ሁለቱ ግን ይቋቋሙታል፥ በሦስትም የተገመደ ገመድ በፍጥነት አይበጠስም።
መጽሐፈ መክብብ 4 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ መክብብ 4:1-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች