ኦሪት ዘዳግም 17:14-20

ኦሪት ዘዳግም 17:14-20 መቅካእኤ

“አምላክህ ጌታ ወደሚሰጥህ ምድር ስትገባ፥ በምትወርሳትና በምትቀመጥባት ምድር፥ ‘በዙሪያዬ እንዳሉት አሕዛብ ሁሉ፥ እኔም በላዬ ንጉሥ ላንግሥ’ ብትል፥ ጌታ እግዚአብሔር የሚመርጠውን ንጉሥ በላይህ ልታነግሥ ትችላለህ፤ የምታነግሠውም ከገዛ ወንድሞችህ መካከል እንጂ፥ እስራኤላዊ ወንድምህ ያልሆነውን ባዕድ በላይህ አታንግሥ። ንጉሡም ብዙ ፈረሶችን ለራሱ አያብዛ፤ ወይም ደግሞ ፈረሰኞች ለማብዛት ሕዝቡን ወደ ግብጽ አይመልስ፤ ጌታ፥ ‘በዚያ መንገድ ፈጽሞ አትመለሱ’ ብሎአችኋልና። ልቡ እንዳይስትም ብዙ ሚስቶችን አያግባ፤ ብዙ ብርና ወርቅም አያግበስብስ። “በመንግሥቱ ዙፋን ላይ በሚቀመጥበትም ጊዜ የዚህን ሕግ ቅጅ ከሌዋውያን ካህናት ወስዶ በጥቅል መጽሐፍ ለራሱ ይጻፍ። አምላኩን ጌታን ማክበር ይማር ዘንድ፥ የዚህን ሕግ ቃል ሁሉና ይህን ሥርዓት በጥንቃቄ እንዲከተል ከእርሱ ጋር ይሁን፤ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ያንብበው፤ እርሱና ዘሮቹ በእስራኤል ላይ ረጅም ዘመን እንዲገዙ፥ ከሕጉ ቀኝም ግራም አይበል፤ ራሱን ከሌሎች ወንድሞቹ በላይ የተሻለ አድርጎ አይኩራ።”