መጽሐፈ ባሮክ 6
6
1በእግዚአብሔር ፊት በፈጸማችሁት በደል ምክንያት በባቢሎናውያን ንጉሥ በናቡከደነፆር ተማርካችሁ ወደ ባቢሎን ትወሰዳላችሁ። 2ወደ ባቢሎን በደረሳችሁ ጊዜ እዚያ ብዙ ዓመታት ትቆያላችሁ፥ እስከ ሰባት ትውልድ። ከዚህ በኋላ ወደ ትውልድ ሀገራችሁ በሰላም እንድትሄዱ አደርጋችኋለሁ። 3ሰው በትከሻው የሚሸከማቸው ሕዝቦችን የሚያስፈሩ፥ በብር፥ በወርቅ፥ በእንጨት የተሠሩትን ጣዖቶች በባቢሎን ታያላችሁ። 4በዚያን ጊዜ ተጠንቀቁ፥ እናንተ በምንም ዓይነት የሌላ አገር ሰዎችን እንዳትመስሉ፥ የእነርሱን አማልክቶቻቸውን አትፍሩ፥ 5በጣዖቶቹ ፊትና ኋላ ሰዎች ሲሰግድ ስታዩ አትደንግጡ፥ ይልቁንም በልባችሁ “ጌታ ሆይ አንተን እናመልካለን” በሉ። 6ምክንያቱም የእኔ መልአክ ከእናንተ ጋር ነው። ሕይወታችሁ በእርሱ ጥላ ሥር ነው። 7በእርግጥ የእነዚህ ጣዖቶች ምላስ ተጠርቦ የተሠራው በአንድ ሠራተኛ ነው፥ እውነት ነው፥ ጣዖቶች በወርቅና በብር ተለብጠው ተሠርተዋል፥ ነገር ግን የውሸት ናቸው፥ መናገርም አይችሉም። 8ማጌጥን እንደምትወድ ልጃገረድ እነዚህ ሰዎችም ወርቅ ይወስድና 9በአማልክቶቻቸው ራስ ላይ ዘውድ ይደፋሉ። እንዲያውም ካህናት እንኳ ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ወርቁንና ብሩን ይወስዳሉ፥ 10ወርቁንና ብሩን በጠላቶቻቸው ቤት ለሚያገለግሉ ሴተኛ አዳሪዎችም እስከ መስጠት ይደርሳሉ፥ እነዚህን የብር፥ የወርቅና የእንጨት ጣዖቶች እንደ ሰዎች ያለብሷቸዋል። 11የከፋይ ካባ የደረቡ እንኳን ቢሆኑም ጣዖቶቹ እራሳቸውን ከመዛግና ከመበላሽት፥ ከሚቦሮቡሩአቸው ትሎች አያድኑም፥ 12በመኖሪያቸው የቤተ መቅደሱ አቧራ ፊታቸውን ስለማያለብሰው ሁልጊዜም አቧራው ከፊታቸው ላይ መጠረግ አለበት። ጣዖቱ የአንድ አውራጃ ገዢ ሆኖ በትረ መንግሥትን ጨብጦ፥ ነገር ግን ሥልጣኑን የሚፈታተነውን ሰው በሞት መቅጣት የሚሳነውን ሰው ይመስላል። 13በቀኝ እጅ ሰይፍና መጥረቢያ ይይዛል። ግን በጦርነት እና ሽፍታ በሚመጣበት ጊዜ ለመከላከያ አይጠቅሙትም። 14አምላክ አለመሆናቸ በዚህ ይታወቃል፥ ስለዚህ አትፍሩአቸው። 15እንስራ ከነቃ ጥቅም እንደሌለው ሁሉ፥ 16በቤተ መቅደስ የተኰለኰሉ አማልክትም እንደዚሁ ናቸው፥ ሰው ሲራመድ በሚነሣው አቧራ የተሸፈኑ ናቸው፥ 17ንጉሥን በመስደቡ ሞት የተፈረደበት ሁሉ በእስር ቤት እንደሚዘጋበት እንዲሁም የጣዖት አገልጋዮች እነዚህ ጣዖቶች በሌቦች እንዳይዘረፉ የጣዖት ቤቶችን በመዝጊያዎች፥ በቁልፎች፥ በብረት ዘንጐች አጥብቀው ይዘጋሉ። 18የጣዖት አገልጋዮቹ ለራሳቸው ከሚገባቸው በላይ ለጣዖቶቹ በርካታ መቅረዞች ያበራሉ፤ ነገር ግን ጣዖቶቹ አንዳቸውም አያዩም። 19በጣዖት ቤቱ እንደሚገኘው፥ ውስጡ በምስጥ እንደተበላው ግንድ ይመስላሉ፥ ከምድር የሚመጣው ምስጥ እነሱን፥ ልብሳቸውንም ይበላል፤ እነሱ አይሰሙትም። 20ከጣዖት ቤቱ በሚወጣው ጢስ ፊቱን አክስሎታል። 21በአካላቸውና በራሳቸው ላይ የሌሊት ወፎችና ንቦች ያርፋሉ፤ ድመቶችም እንዲሁ፥ 22አምላክ አለመሆናቸውን የምታውቁት በዚህ ነው፤ ስለዚህ አትፍሩአቸው። 23እነርሱን ለማሳመር በእነርሱ ላይ የተለበጠው ወርቅም ቆሻሻውን ሰው ካልወለወለው እነሱ አጽድተው ንጹሕ ሊያደርጉት አይችሉም፤ ሊሠሩአቸው በብረት ማቅለጫ ውስጥ ሲያስገቧቸውም አይሰሙም ነበረ። 24ምን ያክል ውድ ዋጋ ቢከፈልባቸውም እስትፋስም ሆነ ሕይወት ፈጽሞ የለባቸውም፥ 25መራመድ ስለማይችሉ ሰው በትከሻው ይሸከማቸዋል። ይህም ምን ያህል ተስፋ አስቆራጭ እንደ ሆኑ ያሳያል። ቢወድቁ እንኳ የሚያነሳቸውን አምላኪዎቻቸውን ምን ያህል ያሳፍሩአቸዋል፥ 26አንዴ ከቆሙ በራሳቸው መነቃነቅ አይችሉም፥ እራሳቸውን ማስተካከል አይችሉም፥ ለእነርሱ የሚቀርብ መሥዋዕት ለሙታን እንደሚቀርብ ያህል ነው። 27ጣዖቶች የሚቀርቡትን ምንም ዓይነት መሥዋዕቶች፥ የጣዖት አገልጋዮቹ ሸጠው ገንዘቡን ለግላቸው ያደርጉታል፤ ሚስቶቻቸውም እንዲሁ ደግሞ የትርፉን ከፊል ይወስዳሉ፤ ነገር ግን ለድሆችና ረዳት ለሌላቸው ምንም አይለግሱም፤ 28በወር አበባዋ ጊዜ ያለች፥ እንዲሁም እመጫት ሴት ለጣዖቶች የቀረቡትን መሠዋዕቶች ይነካሉ። ይህን ሁሉ ስትመለከቱ አምላክ አለመሆናቸውን ስለምታውቁ አትፍሩአቸው። 29እነኚህን የብር የወርቅ፥ የእንጨት አማልዕክት የሚያገለግሏቸው ሴቶች ከሆኑ ታዲያ እንዴት ተብሎ አምላክ ይባላሉ? 30የጣዖት አገልጋዮች የተቀደደ ልብስ ለብሰው፥ ራሳቸውንና ጢማቸውን ሳይሸፍኑ በቤተ መቅደሱ ይቀመጣሉ፥ 31በቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ እንደሚያደርጉት ሆነው በጣዖቶቻቸው ፊት ያጓራሉ፥ ይጮሃሉ። 32የጣዖት አገልጋዮቹ የጣዖቶቹን ልብስ ወስደው ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን ያለብሳልሉ። 33ደግ ቢደረግላቸው ወይም ክፉ ሲደረግባቸው እነዚህ ጣዖቶች መልሰው ብድር መክፈል አይችሉም፤ ንጉሥ መሾም ወይም መሻር እንደማይችሉ ሁሉ ሀብትንና ገንዘብንም ማከፋፈል ይሳናቸዋል። 34ሰው በመሐላ የገባላቸውን ቃል ሳይፈጽመው ቢቀር አይተሳሰቡትም። 35ማንንም ከሞት አያድኑም፤ ደካማውን ከኃይለኛ ሰው አያድኑትም፥ 36የዕውሩን ዐይን አያበሩም፤ በመከራ ላይ የሚገኘውን ሰው ከመከራ አያወጡትም፤ 37ለመበለቶች አይራሩም፤ ወላጆች ለሞቱበት ልጅ መልካም ነገር አያደርጉለትም። 38በወርቅና በብር የተለበጡ እነዚህ የእንጨት አማልዕክቶች ከተራራ ከወደቀ ሥር ዓለት አይሻሉም፤ የሚያገለግሏቸውም ሰዎች እፍረትን ያከናነባሉ። 39ታዲያ እንዴት ተደርጐ አምላክ ናቸው ለማለት ይቻላል? 40ከለዳውያን (ባቢሎናውያን) ራሳቸው ያዋርዷቸዋል፤ መናገር የማይችል ሰው ሲያገኙ ወደ ተባለው ጣዖት ይወስዱታል፤ ጣዖቱ የመናገርን ስጦታ መስጠት እንደሚችል፤ ችግሩ እንደሚገባው ቆጥረው ወደ እሱ ፊት ያቀርቡታል። 41ከዚህ በመነሣት አማልክቱን መተው እንደሚገባቸው አይረዱም፤ የአመለካከት አድማስ ማነስ የሚያሳየው ይህንኑ ነው። 42ሴቶች ገመድ ታጥቀው ገለባውን እንደ ዕጣን ለማጨስ በመንገድ ላይ ይቀመጣሉ፤ 43ከነኝህም ሴቶች መካከል አንዲቱ በአንድ መንገደኛ ተወስዳ ግንኙነት ብታደርግ ከሌሎቹ ሁሉ ገመድን በማስበጠስ እራሷን የተሻለች አድርጋ ታቀርባለች። 44ምንም ቢደረግላቸው ድርጊቱ ውሸት ነው። ታዲያ እንዴት አምላክ ናቸው ይባላሉ? 45በእንጨት ጠራቢዎችና በወርቅ አፍሳሾች የተሠሩ ናቸው፥ እነርሱ ባለሙያዎቹ እንደ ፈለጉት ይሆናሉ እንጂ ሌላ ነገር መሆን አይችሉም። 46እነዚህ የሠሩአቸው ሰዎች እንኳ ረጅም ዕድሜ አይኖሩም። 47እንዴት ታዲያ በነሱ የተሠሩ ነገሮች አምላክ መሆን ይችላሉ? ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ለትውልዳቸው ውሸትንና እፍረትን ይተዋሉ። 48ጦርነትና ችግር ሲመጣ የጣዖቱ ካህናት እነዚህን ጣዖቶች ይዘው የት መደበቅ እንደሚገባቸው እርስ በእርሳቸው ይመካከራሉ። 49ራሳቸውን ከጦርነትና ከችግር ማዳን የማይችሉትን እንዴት አምላክ አለመሆናቸውን ማወቅ ያቅታቸዋል? 50በወርቅና በብር የተለበጡ የእንጨት ዕቃዎች ናቸው፤ ውሸት ብቻ መሆናቸው በዚህ ይታወቃል፤ በሰው እጅ የተሠሩ እንጂ አምላክ አለመሆናቸው ለንጉሦችና ለሕዝቦች ሁሉ ግለጽ ይሆናል፤ በነሱ ምንም የአምላክ ሥራ አለመኖሩ ግልጽ ይሆናል። 51ታዲያ እነሱ አምላክ አለመሆናቸውን ለመቀበል የማይገደድ ማነው? 52ለአንድ አገር ንጉሥ አይሾሙለትም፤ ለሰዎች ዝናብም አያወርዱም። 53ምንም ኃይል ስለ ሌላቸው እነሱን የሚመለከቱ ጉዳዮችን መመልከትና መቆጣጠርም አይችሉም፥ ክፉ ነገር የተሠራበትንም ሰው አይረዱም። 54በእነዚህ በወርቅና በብር በተለበጡ የእንጨት ጣዖቶች ቤተ መቅደስ ላይ እሳት ቢወድቅ፥ የጣዖቶቹ አገልጋዮች ሸሽተው ያመልጣሉ፤ እነርሱ ግን በእሳት ውስጥ እንደሚገኙ ምሰሶ በሙሉ ተቃጥለው ያልቃሉ። 55ንጉሥን ወይም ጠላቶችን መከላከል አይችሉም፤ 56ታዲያ እነሱን አምላክ ናቸው ብሎ መቀበል እንዴት ይቻላል? 57በብርና በወርቅ የተለበጡ የእንጨት ጣዖቶች ከሌባም ሆነ ከወንበዴዎች ራሳቸውን አያድኑም፤ ጉልበተኞች ወርቃቸውንና ብራቸውን ቢወስዱባቸውና የለበሱትም ቢገፏቸው ራሳቸውን እንኳን ከዚህ ጥቃት ለማዳን ምንም ኃይል የላቸውም። 58እንደ እነዚህ የውሸት አማልክት ከመሆን ይልቅ ጀግንነቱን እንደሚያሳይ ንጉሥ፥ በቤት ውስጥ ባለቤቱ የሚጠቀምበት ጠቃሚ እንስራ መሆን ይመረጣል። ወይም ደግሞ በውስጥ ያለውን ነገር የሚጠብቅ የቤት መዝጊያ ይሻላል፥ ወይም ከእነዚህ ከውሸት ጣዖቶች ይልቅ በቤተ መንግሥት የሚገኝ የእንጨት ምሰሶ ይሻላል። 59ብርሃን የሚሰጡት ፀሐይ፥ ጨረቃና ከዋክብት የሚሠሩት ሥራ ተሰጥቷቸዋል፤ ታዛዦችም ናቸው። 60መብረቅም ብልጭ ሲል እንዲሁ መልካም ይታያል፤ 61በተመሳሳይ መልኩ ንፋስ በየሃገሩ ይነፍሳል፤ ደመናዎች መሬት እንዲያካልሉ የተሰጣቸውን ትእዛዝ ይፈጽማሉ። 62ከላይ የወረደው እሳት ጫካውንና ተራራውን እንዲያቃጥል የተሰጠውን ትእዛዝ ይፈጽማል፤ እነኚህ ጣዖቶች ግን ከላይ ከተጠቀሱት ጋር አይወዳደሩም፤ በውበትም ሆነ በኃይል ወይም ለሰዎች መልካም ነገር በማድረግ ምንም ችሎታ የላቸውም። 63በመሆኑም እነርሱን አምላክ ብሎ መጥራት ፈጽሞ አይታሰብም፤ ፍርድ መፍረድ ሆነ ማንንም መርዳት አይችሉም። 64እነሱን አምላክ አለመሆናቸውን እወቁ፤ ስለዚህ አትፍሩአቸው። 65እነሱ ንጉሦቹን መርገምም ሆነ መመረቅ አይችሉም፤ 66ለሕዝቦች በሰማይ ላይ ምልክቶች ማሳየት አይችሉም፤ እንደ ፀሐይ ብርሃን መፈንጠቅ ወይም እንደ ጨረቃ ብርሃን ማንጸባረቅ አይችሉም። 67ወደ አንድ መጠጊያ ቦታ ሸሽተው ራሳቸውን በራሳቸው መርዳት የሚችሉ የዱር አራዊቶች ይበልጧቸዋል። 68ስለዚህ በምንም ዓይነት አምላክ ለመሆናቸው ማስረጃ የለም፤ ሰለዚህ አትፍሩአቸው። 69በብርና በወርቅ የተለበጡ የእንጨት ጣዖቶቻቸው በዱባ እርሻ ውስጥ እንደሚገኝ ከምንም እንደሚያድን በሰው ምስል የቆመ የእንጨት ማስፈራሪያ ናቸው። 70ወይም በአትክልት ስፍራ እንደሚገኘውና ማንኛውም ዓይነት ወፍ እንደሚያርፍበት የእሾህ ቁጥቋጦ ናቸው፤ ወይም ደግሞ ጨለማ ውስጥ የተጣለ ሬሳ ይመስላሉ። 71የከፋዩ ልብሳቸው ብልጭልጭነት ሲበላሽ ስታዩ አምላክ አለመሆናቸው ይገባችኋል። በመጨረሻም እነዚህ ዕቃዎች ምስጥ በልቶ ይጨርሳቸውና የአገር ውርደት ይሆናሉ። 72ትክክለኛና ጣዖት የሌለው ሰው ይሻላል፤ ውርደት በፍፁም ወደሱ አይጠጋምና።
Currently Selected:
መጽሐፈ ባሮክ 6: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ