2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 7:8-16

2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 7:8-16 መቅካእኤ

አሁንም አገልጋዬን ዳዊትን እንዲህ በለው፤ ‘የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፤ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ገዥ እንድትሆን ከሜዳ አነሣሁህ፤ ከበግ ጥበቃም ወሰድሁህ፤ በሄድህበት ሁሉ እኔ ከአንተ ጋር ነበርሁ፤ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አስወገድሁልህ፤ አሁንም ስማቸው በምድር ላይ ከገነነው እጅግ ታላላቅ ሰዎች እንደ አንዱ ስምህን ገናና አደርገዋለሁ፤ የራሱ የሆነ መኖሪያ እንዲኖረውና ከእንግዲህ ወዲያ እንዳይናወጥ፥ ለሕዝቤ ለእስራኤል ቦታ እሰጠዋለሁ፤ አጸናዋለሁም። ከእንግዲህ ወዲህ ክፉ ሕዝብ አይጨቁነውም፤ ከዚህ በፊት እንደ ሆነው፥ ለሕዝቤ ለእስራኤል መሪዎች ከሾምሁለት ጊዜ አንሥቶ እንዳደረጉበት ከእንግዲህ አያደርጉበትም፤ ከጠላቶችህ ሁሉ አሳርፍሃለሁ። ከዚህም በላይ ጌታ ራሱ ቤት እንደሚሠራልህ ይነግርሃል፤ ዕድሜህን ጨርሰህ ከአባቶችህ ጋር በምታንቀላፋበት ጊዜ፥ በእግርህ እንዲተካ ከአብራክህ የተከፈለ ዘር አስነሣልሃለሁ፤ መንግሥቱንም አጸናለሁ። ለስሜ ቤት የሚሠራ እርሱ ነው፤ እኔም የመንግሥቱን ዙፋን ለዘለዓለም አጸናለሁ። አባት እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጄ ይሆናል። በደል በሚፈጽምበትም ጊዜ ሰዎች በሚቀጡበት በትር እቀጣዋለሁ፤ የሰው ልጆችም በዐለንጋ እንደሚገረፉ እገርፈዋለሁ። ከአንተ በፊት ካስወገድሁት ከሳኦል ምሕረቴን እንዳራቅሁ ከእርሱ ግን አላርቅም። ቤትህና መንግሥትህ በፊቴ ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል፤ ዙፋንህም ለዘለዓለም የጸና ይሆናል።’ ”