በዳዊት ዘመነ መንግሥት፥ በተከታታይ ለሦስት ዓመት ራብ ሆነ፤ ስለዚህ ዳዊት ጌታን ጠየቀ፤ ጌታም፥ “ሳኦል ገባዖናውያንን ስለ ገደለ፥ እርሱና ቤቱ የደም ዕዳ አለባቸው” አለ። ንጉሡም ገባዖናውያንን ጠርቶ አነጋገራቸው። ገባዖናውያን ከአሞራውያን የተረፉ እንጂ ከእስራኤል ወገን አልነበሩም፤ እስራኤላውያን ሊጠብቋቸው ቢምሉላቸውም፥ ሳኦል ግን ለእስራኤልና ለይሁዳ ካለው ቅናት የተነሣ ሙሉ በሙሉ ሊያጠፋቸው ፈልጎ ነበር፤ ዳዊትም ገባዖናውያንን፥ “ምን ላድርግላችሁ? የጌታን ርስት ትባርኩ ዘንድ ማስተሰረያውን ምን ማድረግ አለብኝ?” ሲል ጠየቃቸው። ገባዖናውያንም፥ “በእኛና በሳኦል ወይም በእኛና በቤቱ መካከል ያለው የብርና የወርቅ ጉዳይ አይደለም፥ እንዲሁም ከእስራኤል ማንንም ለመግደል መብት የለንም” ብለው መለሱለት። ዳዊትም፥ “ታዲያ ምን ላድርግላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም፥ “እንድንፈራርስና በእስራኤልም ውስጥ በየትኛውም ስፍራ እንዳንኖር ካጠፋንና ደባ ከፈጸመብን ሰው ከእርሱ ዘሮች ሰባት ወንዶች ልጆች ይሰጠን፤ እኛም ከጌታ በተመረጠው በሳኦል አገር በጊብዓ በጌታ ፊት እንስቀላቸው” ብለው መለሱለት። ስለዚህ ንጉሡ፥ “እሺ! እሰጣችኋለሁ” አለ። ንጉሥ ዳዊት በራሱና በሳኦል ልጅ በዮናታን መካከል በጌታ ፊት ስላደረጉት መሐላ ሲል የሳኦልን ልጅ፥ የዮናታንን ልጅ መፊቦሼትን ከሞት አተረፈ። ነገር ግን ንጉሡ የአያ ልጅ ሪጽፋ ለሳኦል የወለደቻቸውን ሁለቱን ወንዶች ልጆች አርሞኒንና መፊቦሼትን፤ የሳኦል ልጅ ሜራብ ለመሖላታዊው ለባርዚላይ ልጅ ለአድሪኤል የወለደችለትን አምስት ወንዶች ልጆች ጭምር ወሰደ፤ ከዚያም ለገባዖናውያን አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱም ገድለው በኰረብታው ላይ በጌታ ፊት ሰቀሏቸው። ሰባቱም በአንድነት ሞቱ፤ የተገደሉትም እህል በሚታጨድበት ወራት በገብሱ መከር መጀመሪያ ነበር። የአያ ልጅ ሪጽፋ ማቅ ወስዳ፥ በቋጥኝ ላይ ለራሷ አነጠፈች፤ ከመከር ወቅት መጀመሪያ አንሥቶ ዝናብ ከሰማይ በሬሳዎቹ ላይ እስከወረደ ጊዜ ድረስ ቀን የሰማይ ወፎች ሌሊት የዱር አራዊት እንዲነኳቸው አልፈቀደችም፤ የሳኦል ዕቁባት የአያ ልጅ ሪጽፋ ያደረገችውን ዳዊት በሰማ ጊዜ፥ ዳዊት ሄዶ፥ ሳኦልን በጊልቦዓ በገደሉ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን ከሰቀሉአቸው ስፍራ ከቤት ሻን አደባባይ ከሰረቁት ከያቤሽ ገለዓድ ሰዎች የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አጥንት ወሰደ፥ የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን ዐፅም ከዚያ አምጥቶ፥ የእነዚያን የተሰቀሉትን ሰዎች ዐፅምም ሰበሰቡ። የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን ዐፅም በብንያም አገር ጼላ በተባለ ስፍራ በሳኦል አባት በቂስ መቃብር ቀበሩት፤ ንጉሡ ያዘዘውንም ሁሉ አደረጉ። ከዚያ በኋላም ስለ ምድሪቱ የቀረበውን ጸሎት እግዚአብሔር ሰማ።
2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 21 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 21:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች