ንጉሥ ዳዊት ወደ ባሑሪም ሲደርስ፥ ከሳኦል ቤተ ዘመድ የሆነ አንድ ሰው ወጣ፤ ስሙ ሺምዒ ሲሆን የጌራ ልጅ ነው፤ እየተራገመም ወደ እርሱ ይመጣ ነበር። በንጉሡም ቀኝና ግራ ሕዝቡ ሁሉና ኀያላኑ ሁሉ ቢኖሩም እንኳ፥ ወደ ዳዊትና ወደ ንጉሥ ዳዊት አገልጋዮችም ድንጋይ ይወረውር ነበር፤ ሺምዒ እንዲህ ብሎ ይራገም ነበር፤ “ውጣ! ከዚህ ውጣ! አንተ የደም ሰው፤ አንተ ምናምንቴ፤ መንግሥቱን የወሰድክበትን የሳኦልን ቤተሰቡ ደም ሁሉ ጌታ ወደ አንተው እየመለሰው ነው። ጌታ መንግሥትህን ለልጅህ ለአቤሴሎም አሳልፎ ሰጥቶታል፤ አንተ የደም ሰው ስለሆንህ እነሆ፥ መጥፊያህ ደርሶአል።” ከዚያም የጽሩያ ልጅ አቢሳ ንጉሡን፤ “ይህ የሞተ ውሻ፥ ንጉሥ ጌታዬን እንዴት ይራገማል? ልሂድና ራሱን ልቁረጠው” አለ። ንጉሡ ግን፥ “እናንት የጽሩያ ልጆች እኔ ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? ጌታ፥ ‘ዳዊትን ርገመው’ ብሎት የሚረግመኝ ከሆነ፥ ‘ይህን ለምን አደረግህ’ ብሎ ማን ሊጠይቀው ይችላል?” አለው። ከዚያም ዳዊት አቢሳንና አገልጋዮቹን ሁሉ እንዲህ አላቸው፤ “ከአብራኬ የወጣ ልጅ ሕይወቴን ሊያጠፋት ከፈለገ፥ ይህ ብንያማዊ ቢያደርገው ምን ያስደንቃል? ስለዚህ ተዉት፤ ጌታ በል ብሎት ነውና ይራገም፤ ጌታ ምናልባት በዚህ ቀን መከራዬን አይቶ ስለ እርግማኑ መልካም ይመልስልኛል” አላቸው። ስለዚህም ዳዊትና ሰዎቹ መንገዳቸውን ቀጠሉ፤ ሺምዒ በተራራው አጠገብ በእርሱ ትይዩ እየሄደ ይራገም ድንጋይም ይወረውር፥ ዐፈርም ይበትን ነበር።
2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 16 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 16:5-13
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች