2ኛ የጴጥሮስ መልእክት 2:1-9

2ኛ የጴጥሮስ መልእክት 2:1-9 መቅካእኤ

ነገር ግን ሐሰተኞች ነቢያት ደግሞ በሕዝቡ መካከል እንደ ነበሩ፤ እንዲሁም በመካከላችሁ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይኖራሉ፤ እነርሱም ጥፋትን የሚያስከትሉ ትምህርቶች አስርገው በማስገባት የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው፥ በራሳቸው ላይ ፈጣን ጥፋትን ያመጣሉ። እንዲሁም ብዙዎች ጸያፍ ምግባራቸውን ይከተሏቸዋል፤ በእነርሱም ጠንቅ የእውነት መንገድ ይሰደባል። ለገንዘብ ከመስገብገባቸው የተነሣ ራሳቸው ያዘጋጁትን ታሪክ እያወሩ ይበዘብዙአችኋል። ፍርዳቸውም ከብዙ ዘመን በፊት ጀምሮ ተዘጋጅቶላቸዋል፤ ጥፋትም በእርግጥ ይጠብቃቸዋል! እግዚአብሔር ኃጢአትን ላደረጉ መላእክት ሳይራራላቸው ወደ ገሃነም ጥሎ በጨለማ ጉድጓድ ለፍርድ ሊጠበቁ አሳልፎ ከሰጣቸው፥ ለቀደመውም ዓለም ሳይራራ፥ ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን ከሌሎች ሰባት ሰዎች ጋር አድኖ፥ በኀጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውሃ ካወረደ፥ ኃጢአትንም እያደረጉ ላሉት ምሳሌ እንዲሆን፤ የሰዶምንና ገሞራን ከተማዎች አመድ እስኪሆኑ ድረስ አቃጥሎ እንዲጠፉ ከፈረደባቸው፥ በዝሙት ሥራቸው ሲሳቀቅ የነበረውን ጻድቅ ሎጥን ካዳነ፤ ያ ጻድቅ ሰው፥ በመካከላቸው ሲኖር ዕለት ከዕለት የዐመፀኞችን ሴሰኛ ኑሮ እያየና እየሰማ በክፉ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን ቢያስጨንቅም፤ እንግዲህ እነሆ፥ ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንደሚያድናቸው፥ እንዲሁም በደለኞችን እንዴት በቅጣት ስር ለፍርድ ቀንም ጠብቆ እንደሚያቈያቸው ያውቃል።