2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 28

28
አካዝ መንገሡ
1አካዝ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሃያ ዓመት ጎልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ዐሥራ ስድስት ዓመት ነገሠ፤ እንደ አባቱም እንደ ዳዊት በጌታ ፊት ቅን ነገር አላደረገም። 2ነገር ግን በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፥ ደግሞም ለበኣሊም ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎችን ሠራ። 3ደግሞም በሄኖም ልጅ ሸለቆ ውስጥ ዐጠነ፤ ጌታ ከእስራኤል ልጆች ፊት እንዳሳደዳቸው እንደ አሕዛብም ክፉ ልማድ ልጆቹን በእሳት አቃጠለ። 4በኮረብታው መስገጃዎችና በተራሮች ላይ በለመለመውም ዛፍ ሁሉ በታች ይሠዋና ያጥን ነበር።
ሶርያ እስራኤልን ድል መነንሣቱ
5 # 2ነገ. 16፥5፤ ኢሳ. 7፥1። ስለዚህ ጌታ አምላኩ በሶርያ ንጉሥ እጅ አሳልፎ ሰጠው፤ ሶሪያውያንም ድል አደረጉት፥ ከእርሱም ብዙ ምርኮኞች ወስደው ወደ ደማስቆ አመጡ። ደግሞም በእስራኤል ንጉሥ እጅ አሳልፎ ሰጠው፤ እርሱም በታላቅ ውግያ ድል አደረገው። 6የአባቶቻቸውንም አምላክ ጌታን ትተው ነበርና የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በአንድ ቀን ከይሁዳ መቶ ሃያ ሺህ ገደለ፤ ሁሉም ጽኑዓን ነበሩ። 7ከኤፍሬም ወገን የነበረው ኃያል ሰው ዝክሪ የንጉሡን ልጅ መዕሤያንና የቤቱን አዛዥ ዓዝሪቃምን፥ ለንጉሡም በማዕረግ ሁለተኛ የሆነውን ሕልቃናን ገደለ።
የዖዴድ ጣልቃ ገብነት
8የእስራኤል ልጆች ከወንድሞቻቸው ሁለት መቶ ሺህ ሴቶችን፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ማረኩ፥ ብዙም ምርኮ ከእነርሱ ወስደው ወደ ሰማርያ አገቡ። 9በዚያም ዖዴድ የተባለ የጌታ ነቢይ ነበረ፤ ወደ ሰማርያም የሚመጣውን ጭፍራ ሊገናኘው ወጣ፥ እንዲህም አላቸው፦ “እነሆ፥ የአባቶቻችሁ አምላክ ጌታ ይሁዳን ስለ ተቈጣ በእጃችሁ አሳልፎ ሰጣቸው፥ እናንተም ወደ ሰማይ በሚደርስ ቁጣ ገደላችኋቸው። 10አሁንም የይሁዳና የኢየሩሳሌም ልጆች ባርያዎች ሆነው እንዲገዙላችሁ ታስባላችሁ፤ ነገር ግን አምላካችሁን ጌታን የበደላችሁት በደል በእናንተ ዘንድ የለምን? 11አሁንም ስሙኝ፤ የጌታ ቁጣ በላያችሁ ነድዶአልና ከወንድሞቻችሁ የወሰዳችኋቸውን ምርኮኞች መልሱ።” 12ደግሞም ከኤፍሬም ልጆች አለቆች የዮሐናን ልጅ ዓዛርያስ፥ የምሺሌሞትም ልጅ በራክያ፥ የሰሎምም ልጅ ይሒዝቅያ፥ የሐድላይም ልጅ ዓሜሳይ ከጦርነት በተመለሱት ላይ ተቃወሙአቸው። 13እነርሱም እንዲህ አሉአቸው፦ “በጌታ ፊት በእኛ ላይ በደል ታመጡብናላችሁና፥ ኃጢአታችንንና በደላችንን ታበዙብናላችሁና የተማረኩትን ወደዚህ አታግቡ፤ በደላችን ታላቅ ነውና፥ የመቅሰፍቱም ቁጣ በእስራኤል ላይ ነውና።” 14ተዋጊዎቹም ምርኮኞቹንና ምርኮውን በአለቆችና በጉባኤው ሁሉ ፊት ተው። 15በስማቸውም የተጻፉ ሰዎች ተነሥተው ምርኮኞቹን ወሰዱ፥ በመካከላቸውም ራቁታቸውን ለነበሩት ሁሉ ከምርኮው አለበሱአቸው፥ አጎናጸፉአቸውም፥ ጫማም በእግራቸው አደረጉላቸው፥ መገቡአቸውም፥ አጠጡአቸውም፥ ቀቡአቸውም፤ ደካሞቹንም ሁሉ በአህዮች ላይ አስቀመጡአቸው፥ ዘንባባም ወዳለበት ከተማ ወደ ኢያሪኮ ወደ ወንድሞቻቸው አመጡአቸው፤ ወደ ሰማሪያም ተመለሱ።
አሦር ይሁዳን ለመርዳት እምቢ ማለትዋ
16በዚያን ጊዜም ንጉሡ አካዝ እርዳታ ፈልጎ ወደ አሦር ንጉሥ ላከ፤ 17የኤዶምያስ ሰዎች ዳግመኛ መጥተው፥ ይሁዳንም መትተው ብዙ ምርኮኛ ወስደው ነበርና። 18ደግሞም ፍልስጤማውያን በቈላውና በደቡብ በኩል ባሉት በይሁዳ ከተሞች አደጋ ጥለው ነበር፤ ቤትሳሚስንና ኤሎንን፥ ግዴሮትንም፥ ሦኮንና መንደሮችዋን፥ ተምናንና መንደሮችዋን፥ ጊምዞንና መንደሮችዋን ወስደው በዚያ ተቀምጠው ነበር። 19የይሁዳም ንጉሥ አካዝ ጌታን ክዷልና፥ ከእርሱም እጅግ ርቋልና ጌታ ስለ እርሱ ይሁዳን አዋረደው። 20የአሦርም ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር መጥቶ አስጨነቀው እንጂ አልረዳውም። 21አካዝም ከጌታ ቤት ከንጉሡና ከአለቆቹም ቤት እኩሌታውን ገፈፈ፥ ለአሦርም ንጉሥ ሰጠ፤ ነገር ግን እንዲህ ማድረጉ አንዳች አልጠቀመውም።
የአካዝ መክዳትና መሞት
22ይህም ንጉሥ አካዝ በተጨነቀ ጊዜ ጌታን መበደል አበዛ። 23ድል ለነሡትም ለደማስቆ አማልክት፦ “የሶሪያን ነገሥታት አማልክት ረድተዋቸዋልና እኔን እንዲረዱኝ እሠዋላቸዋለሁ” ብሎ ሠዋላቸው። ነገር ግን ለእርሱና ለእስራኤል ሁሉ እንቅፋት ሆኑ። 24አካዝም የጌታን ቤት ዕቃዎች ሁሉ ወስዶ ሰባበራቸው፥ የጌታንም ቤት ደጅ ቈለፈ፤ በኢየሩሳሌምም ማዕዘን ሁሉ መሠዊያ ሠራ። 25በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ለሌሎች አማልክት ለማጠን የኮረብታ መስገጃዎች አሠራ የአባቶቹንም አምላክ ጌታን አስቈጣ። 26የቀረውም ነገርና ሥራው ሁሉ፥ የፊተኛውና የኋለኛው፥ እነሆ፥ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል። 27#ኢሳ. 14፥28።አካዝም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በከተማይቱም በኢየሩሳሌም ቀበሩት፤ ነገር ግን ወደ እስራኤል ነገሥታት መቃብር አላገቡትም፤ ልጁም ሕዝቅያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ