2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 16:1-14

2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 16:1-14 መቅካእኤ

አሳ በነገሠ በሠላሳ ስድስተኛው ዓመት የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ በይሁዳ ላይ ዘመተ፥ ወደ ይሁዳም ንጉሥ ወደ አሳ ማንም መውጣትና መግባት እንዳይችል ራማን ሠራ። አሳም ከጌታ ቤትና ከንጉሡ ቤት መዝገብ ብርና ወርቅ ወስዶ በደማስቆ ወደ ተቀመጠው ወደ ሶሪያ ንጉሥ ወደ ወልደ አዴር እንዲህ ብሎ ላከ፦ “በአባቴና በአባትህ መካከል እንደነበረው ቃል ኪዳን በእኔና በአንተ መካከል ይሁን፤ እነሆ፥ ብርና ወርቅ ልኬልሃለሁ፤ እርሱ ከእኔ ዘንድ እንዲርቅ ሄደህ ከእስራኤል ንጉሥ ከባኦስ ጋር ያለህን ቃል ኪዳን አፍርስ።” ወልደ አዴር ንጉሡን አሳን እሺ አለው፥ የሠራዊቱንም የጦር አዛዦች በእስራኤል ከተሞች ላይ ላከ፤ እነርሱም ዒዮንንና ዳንን፥ አቤልማይምንና ለንፍታሌም እንደ ግምጃ ቤት የሚያገለግሉትን ከተሞች ሁሉ ያዙ። ባኦስም በሰማ ጊዜ ራማን መሥራት ተወ፥ ሥራውንም አቋረጠ። ንጉሡም አሳ የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ሰበሰበ፤ እነርሱም ባኦስ ይሠራበት የነበረውን የራማን ድንጋይና እንጨት ወሰዱ፥ እርሱም ጌባንና ምጽጳን ሠራበት። በዚያን ጊዜም ባለ ራእዩ ዓናኒ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “በሶሪያ ንጉሥ ታምነሃልና፥ በአምላክህም በጌታ አልታመንህምና ስለዚህ የሶርያ ንጉሥ ሠራዊት ከእጅህ አምልጦአል። ኢትዮጵያውያንና የልብያ ሰዎች እጅግ ብዙ ሰረገሎችና ፈረሰኞች የነበሩአቸው እጅግ ታላቅ ሠራዊት አልነበሩምን? በጌታ ስለ ታመንህ በእጅህ አሳልፎ ሰጣቸው፥ ጌታ ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ለማጽናት ዐይኖቹ በምድር ሁሉ ይመለከታሉና። እንግዲህ አሁን የሞኞችን ተግባር ፈጽመሃል። ስለዚህም ከዛሬ ጀምሮ ጦርነት ይደረግብሃል።” አሳም በባለ ራእዩ ላይ ተቈጣ፤ ስለዚህም ነገር ተቈጥቶአልና በቊራኛ አስሮ በወህኒ ቤት አኖረው፤ በዚያን ጊዜም አሳ፥ ከሕዝቡ አያሌ ሰዎችን አሠቃየ። የአሳም የፊተኛውና የኋለኛው ነገር፥ እነሆ፥ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል። በነገሠም በሠላሳ ዘጠኝኛው ዓመት አሳ እግሩን ታመመ፤ ደዌውም ጸናበት፤ ነገር ግን በታመመ ጊዜ ባለ መድኃኒቶችን እንጂ ጌታን አልፈለገም። አሳም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በነገሠም በአርባ አንደኛው ዓመት ሞተ። ለእርሱም ለራሱ በሠራው መቃብር በዳዊት ከተማ ቀበሩት፤ በቀማሚ ብልሃት የተሰናዳ ልዩ ልዩ መልካም ሽቶ በተሞላው አልጋ ላይም አኖሩት፤ እጅግም ታላቅ የሆነ የመቃብር ወግ አደረጉለት።