1ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 2:13-20

1ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 2:13-20 መቅካእኤ

ስለዚህም የመልእክትን ቃል፥ እርሱም የእግዚአብሔርን ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፥ በእውነት እንዳለ በእናንተ በአማኞች ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት፥ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን። እናንተ ወንድሞች ሆይ! በይሁዳ የሚኖሩትን በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉትን የእግዚአብሔርን ማኅበሮች የምትመስሉ ሆናችኋልና፤ እነርሱ ከአይሁድ መከራ እንደ ተቀበሉ፥ እናንተ ደግሞ ያንን መከራ ከወገኖቻችሁ ተቀብላችኋልና። እነዚያም ጌታን ኢየሱስንና ነቢያትን ገደሉ፤ እኛንም ደግሞ አሳደዱ፤ እግዚአብሔርንም ደስ አያሰኙም፤ ሰዎችንም ሁሉ ይቃወማሉ፤ ለአሕዛብ እንዳንናገር በመከልከል እነርሱ እንዳይድኑ ያደርጋሉ፤ በዚህም ያለማቋረጥ የኃጢአታቸውን መስፈርያ ይሞላሉ፤ ነገር ግን በመጨረሻ የእግዚአብሔር ቁጣው ይመጣባቸዋል። እኛ ግን ወንድሞች ሆይ! በልብ ሳይሆን በአካል ለጥቂት ጊዜ ብናጣችሁም፥ በብዙ ናፍቆት ግን ፊታችሁን ለማየት እጅግ ጓጓን፤ ወደ እናንተ ልንመጣ ፈልገን ነበርና፤ በእርግጥም እኔ ጳውሎስ አንድና ሁለት ጊዜ ሞክሬ ነበር፥ ሰይጣን ግን መሰናክል ሆነብን። ጌታችን ኢየሱስ በሚመጣበት ጊዜ በፊቱ የተስፋችን ወይም የደስታችን ወይም የመመክያችን አክሊል ምንድነው? እናንተ አይደላችሁምን? እናንተ ክብራችን ደስታችንም ናችሁና።