ከዚያም ሰሎሞን የእስራኤል ሕዝብ ሁሉም በተገኙበት ተነሥቶ በጌታ መሠዊያ ፊት ለፊት ቆመ፤ እጆቹንም ወደ ሰማይ ዘረጋ። እንዲህም አለ፦ “የእስራኤል አምላክ ጌታ ሆይ! በላይ በሰማይ በታችም በምድር አንተን የሚመስል አምላክ የለም፥ በፍጹም ልባቸው በፊትህ ለሚሄዱ አገልጋዮችህ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ፤ ለአገልጋይህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውንም የተስፋ ቃል የጠበቅህ፥ በአፍህ እንደተናገርከው ሁሉ እነሆ ዛሬ በእጅህ ፈጸምከው። አሁንም የእስራኤል አምላክ ጌታ ሆይ! ለአገልጋይህ ለአባቴ ለዳዊት ‘አንተ በፊቴ ትሄድ እንደነበረው ልጆችህ መንገዳቸውን ቢጠብቁ፥ በፊቴም በቅንነት ቢመላለሱ ከዘርህ በእስራኤል ዙፋን ላይ በፊቴ የሚነግሥ ልጅ መቼም አላሳጣህም’ ስትል የተናገርከውን የተስፋ ቃል ፈጽም! አሁንም የእስራኤል አምላክ ሆይ! አገልጋይህ ለነበረው ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸው የተስፋ ቃል ሁሉ እንዲፈጸም አድርግ። “በውኑ እግዚአብሔር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ ሰማያት፥ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ ሊይዝህ አይችልም፤ እኔ የሠራሁት ይህ ቤተ መቅደስማ ምንኛ ያንስ! አቤቱ ጌታ፥ አምላኬ ሆይ! ወደ አገልጋይህ ጸሎትና ልመና ተመልከት፤ ዛሬም አገልጋይህ በፊትህ የሚጸልየውን ጸሎትና ጥሪውን ስማ። ‘ስሜ ይጠራበታል’ ወዳልከው ስፍራ ወደዚህ ቤት ዐይኖችህ ቀንና ሌሊት ይመልከቱ፤ አገልጋይህም በዚህ ስፍራ የምጸልየውን ጸሎት ስማ። አገልጋይህና ሕዝብህ እስራኤል በዚህ ስፍራ የሚጸልዩትን ልመና ስማ፤ በማደሪያህ በሰማይ ስማን፤ ሰምተህም ይቅር በለን። “አንድ ሰው ባልንጀራውን ቢበድል፥ አለመበደሉን በመሐላ እንዲያረጋግጥ ሲጠየቅ፥ እርሱም መጥቶ በዚህ ቤት በሚገኘው መሠዊያ ፊት መሐላ ቢያደርግ፥ በሰማይ ሆነህ ስማ፥ አድርግም፥ ለአገልጋዮችህም ፍርድን ስጥ፤ በበደለኛውም ላይ ፍረድ፤ ስለአካሄዱም ቅጣው፤ ንጹሑንም ነጻ አውጣው፥ እንደ ጽድቁም ክፈለው። “ሕዝብህ እስራኤል አንተን ስለ በደሉ በጠላቶቻቸው ፊት ድል ቢመቱ፥ ነገር ግን ወደ አንተ ቢመለሱ፥ ስምህንም ቢያከብሩ፥ በዚህም ቤት ቢጸልዩና ቢለምኑህ፥ አንተ በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን ስማ፤ በምርኮ የሚገኙትንም ሕዝብህን ኃጢአት ይቅር በማለት ለቀድሞ አባቶቻቸው ወደ ሰጠሃቸው ምድር መልሳቸው። “አንተን በማሳዘናቸው ምክንያት ዝናብ እንዳይዘንብላቸው አድርገህ በምትቀጣቸው ጊዜ፥ በፈጸሙት በደል በመጸጸት ፊታቸውን ወደዚህ ቤተ መቅደስ መልሰው በትሕትና ቢለምኑህ፥ አንተ በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን ስማ፤ የሚሄዱበትንም መልካም መንገድ በማሳየት የአገልጋዮችህን የእስራኤልን ኃጢአት ይቅር በል፤ ርስት አድርገህ ለሕዝብህ በሰጠሃቸው ምድር ዝናብ እንዲዘንብ አድርግ። “በምድሪቱ ላይ ረሀብ ወይም ቸነፈር ቢመጣ፥ በውርጭ፥ በዋግና በአንበጣ ወይም በኩብኩባ መንጋ ቢትወረር፥ የሕዝብህም ጠላት የአገሩን ቀበሌዎች ከብቦ ቢያስጨንቃቸው፥ መቅሠፍትና ደዌ ሁሉ ቢሆን፥ ልብን የሚያሸብር መራር ኀዘን ደርሶባቸው፥ ከማንም ሰው ወይም ከሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ቤተ መቅደስ እጃቸውን በመዘርጋት በሚጸልዩበት ጊዜ፥ በምትኖርበት በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን ስማ፤ በደላቸውን ይቅር በል፤ እርዳቸው፤ በሰው ልብና አእምሮ ያለውን ሐሳብ ሁሉ መርምረህ የምታውቅ አንተ ብቻ ነህ፤ ስለዚህ ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው መጠን የሚገባውን ዋጋ ስጠው። በዚህም ዓይነት ሕዝብህ ለቀድሞ አባቶቻችን ርስት አድርገህ በሰጠሃቸው ምድር በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ ለአንተ ታዛዦች እንዲሆኑና እንዲያከብሩህ አድርግ። “ከሕዝብህ ከእስራኤል ወገን ያልሆነ፥ ግን ከስምህ ታላቅነት የተነሣ ከሩቅ የመጣ የባዕድ አገር ሰው ቢኖር፥ ሰዎች ከሩቅ የሚመጡት ስለ ታላቁ ስምህ፥ ስለ ጠንካራዪቱ እጅህ፥ ስለ ተዘረጋችው ክንድህ ሰምተው ነውና፤ እንግዳው መጥቶ ወደዚህ ቤተ መቅደስ ቢጸልይ፥ አንተ ጸሎቱን ስማ፤ ሕዝብህ እስራኤላውያን እንደሚያደርጉት በመላው ዓለም የሚኖሩ ሕዝቦች አንተን በማወቅ እንዲታዘዙህና እንዲያከብሩህ አድርግ፤ በምትኖርበት በሰማይ ሆነህ የዚህን ሰው ጸሎት ስማ፤ እንድታደርግለት የሚለምንህንም ሁሉ ፈጽምለት፤ ይህም በሚሆንበት ጊዜ ይህ እኔ የሠራሁት ቤተ መቅደስ የአንተ ስም የሚጠራበት መሆኑን ያውቃሉ። “ጠላቶቻቸውን ለመውጋት እንዲዘምቱ ሕዝብህን በምታዝበት ጊዜ በየትኛውም ስፍራ ሆነው ወደዚህች ወደ መረጥኻት ከተማና እኔ ለአንተ ወደ ሠራሁት ወደዚህ ቤተ መቅደስ ፊታቸውን መልሰው በሚጸልዩበት ጊዜ፥ በሰማይም ሆነህ ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በመስማት ዓላማቸውን ደግፍ። “መቼም በደል የማይሠራ የለምና ሕዝብህ ኃጢአት በመሥራት አንተን ሲያሳዝኑህ፥ አንተም ተቆጥተህ ጠላቶቻቸው ድል እንዲነሡአቸውና ወደ ሌላ አገር ማርከው እንዲወስዱአቸው በምትፈቅድበት ጊዜ፥ ምንም እንኳ ያ አገር ሩቅ ቢሆን፥ ምርኮኞች ሆነው በሚኖሩባት በዚያች አገር ሳሉ ‘ኃጢአት ሠርተናል፤ በድለናል፤ ዐምፀናልም’ ብለው በመናዘዝ ተጸጽተው ንስሓ ቢገቡ፥ ማርከው በወሰዱአቸው በጠላቶቻቸው አገር ሳሉ በፍጹም ልባቸው በእውነትና በቅን መንፈስ ተጸጽተው ንስሓ በመግባት አንተ ለቀድሞ አባቶቻችን ወደ ሰጠሃቸው ወደዚህች ምድር፥ አንተም ወደ መረጥኻት ወደዚህች ከተማና እኔ ለአንተ ወደ ሠራሁት ወደዚህ ቤተ መቅደስ ፊታቸውን መልሰው ቢጸልዩ፥ በመኖሪያህ በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን በመስማት ፍረድላቸው። ኃጢአታቸውንና አንተን ያሳዘኑበትን ዐመፅ ሁሉ ይቅር በል፤ ጠላቶቻቸውም እንዲራሩላቸው አድርግ፤ እነርሱ እኮ እንደ እቶን እሳት ከምታቃጥል ከግብጽ ምድር ያወጣሃቸው ሕዝብህ ናቸው። “በጠሩህም ጊዜ ሁሉ ትሰማቸው ዘንድ ለአገልጋይህና ለሕዝብህ ልመና ዐይኖችህ የተገለጡ ይሁኑ። እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! የቀድሞ አባቶቻችንን ከግብጽ ምድር ባወጣህ ጊዜ ከዓለም ሕዝብ ሁሉ መካከል እስራኤልን የራስህ ሕዝብ እንዲሆን የመረጥከው መሆኑን በአገልጋይህ በሙሴ አማካይነት ተናግረሃል።”
1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 8 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 8:22-53
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች