1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 3:5-15

1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 3:5-15 መቅካእኤ

በዚያች ሌሊት ጌታ በገባዖን ለሰሎሞን በሕልም ተገለጠለትና “ምን እንድሰጥህ ትፈልጋለህ?” አለው። ሰሎሞንም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “አገልጋይህ የነበረው አባቴ ዳዊት ደግ፥ ታማኝና ቅን ሰው በመሆኑ ጽኑ ፍቅርህን ስታሳየው ኖረሃል፤ ዛሬም በእርሱ እግር ተተክቶ በዙፋኑ የሚቀመጥ ልጅ በመስጠት ታላቅና ጽኑ የሆነውን የማያቋርጥ ፍቅርህን ገልጠህለታል። አቤቱ፥ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! እነሆ እኔ በዕድሜ አነስተኛ ነኝ፤ የአመራር ልምድም የለኝም፤ አንተ ግን በአባቴ እግር ተተክቼ እንድነግሥ ፈቃድህ ሆኖአል። እነሆ እኔ የአንተ እንዲሆን በመረጥከውና ከብዛቱ የተነሣ ሊቆጠር በማይችል ሕዝብ መካከል እገኛለሁ። ስለዚህ ክፉውንና በጎውን በመለየት ሕዝብህን በትክክለኛ ፍርድ ለመምራት የሚያስችለኝን ጥበብ ስጠኝ፤ ይህ ካልሆነ ግን ታላቅ ሕዝብህን እንዴት ልመራ እችላለሁ?” ሰሎሞን ይህን በመጠየቁ ጌታን ደስ አሰኘው። እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “ለራስህ ረጅም ዕድሜ ወይም ሀብት ለማግኘት ወይም ጠላቶችህ እንዲጠፉልህ መመኘት ሳይሆን በትክክለኛ ፍርድ ማስተዳደር የምትችልበትን ጥበብ ስለ ጠየቅህ፥ እነሆ የጠየቅኸውን አደርጋለሁ፤ እንዲያውም ማንም ሰው ከዚህ በፊት ካገኘውና ወደፊትም ሊያገኘው ከሚችለው የበለጠ ጥበብንና አስተዋይነትን እሰጥሃለሁ። ከዚህም በላይ አንተ ያልጠየቅከውንም ሁሉ ጨምሬ እሰጥሃለሁ፤ ይኸውም በዘመንህ ማንኛውም ሌላ ንጉሥ ያላገኘውን ብልጽግናና ክብር አበዛልሃለሁ። አባትህ ዳዊት እንዳደረገው በመንገዴ ብትሄድና ለእኔም ብትታዘዝ፥ ሕጌንና ትእዛዞቼንም ብትፈጽም ረጅም ዕድሜ እሰጥሃለሁ።” ሰሎሞን ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ እግዚአብሔር በሕልም ተገልጦ ያነጋገረው መሆኑን ተገነዘበ፤ ከዚህ በኋላ ሰሎሞን ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ ሄደ፤ በጌታ የቃል ኪዳን ታቦት ፊት ቆሞ የሚቃጠል መሥዋዕትንና የኅብረት መሥዋዕት አቀረበ፤ ለባለሟሎቹም ሁሉ ግብዣ አደረገ።