ንጉሥ ሰሎሞን በየዓመቱ ኻያ ሦስት ሺህ ኪሎ ያኽል የሚመዝን ወርቅ ያገኝ ነበር። ይህም ሁሉ ነጋዴዎች ከሚከፍሉት ቀረጥ፥ ከንግድ ከሚገኘው ትርፍ፥ እንዲሁም ከዐረብ ነገሥታትና ከእስራኤል ክፍላተ ሀገር አስተዳዳሪዎች ከሚገባለት ግብር ጋር ተጨማሪ ነበር። ንጉሥ ሰሎሞን ሁለት መቶ ታላላቅ ጋሻዎችን አሠርቶ እያንዳንዱን ጋሻ በሰባት ኪሎ ያኽል ወርቅ አስለበጠው። እንዲሁም ሦስት መቶ ታናናሽ ጋሻዎችን አሠርቶ እያንዳንዱን በሁለት ኪሎ ያኽል ወርቅ አስለበጠው፤ እነዚህንም ሁሉ “የሊባኖስ ደን” ተብሎ በሚጠራው አዳራሽ ውስጥ አኖራቸው። እንዲሁም ንጉሥ ሰሎሞን ከዝሆን ጥርስ አንድ ትልቅ ዙፋን አሠርቶ በንጹሕ ወርቅ አስለበጠው። ወደ ዙፋኑ መወጣጫ ስድስት ደረጃዎች ነበሩ፤ የዙፋኑ ጀርባ ራስጌው ክብ ነበር፤ በዙፋኑ ግራና ቀኝ የክንድ ማሳረፊያዎች ነበሩ፤ በክንድ ማሳረፊያዎቹ ጐን አንዳንድ የአንበሳ ምስሎች ቆመው ነበር። በየአንዳንዱ ደረጃ በሁለት በኩል አንዳንድ የአንበሳ ምስል በድምሩ ዐሥራ ሁለት የአንበሳ ምስሎች ቆመዋል። ይህን የመሰለ ዙፋን በሌላ በየትኛውም አገር ተሠርቶ አይታወቅም። በሰሎሞን ዘመን ብር ምንም ዋጋ ስላልነበረው ሰሎሞን የሚጠጣባቸው ዋንጫዎች ሁሉና “የሊባኖስ ደን” ተብሎ በሚጠራው አዳራሽ ውስጥ የሚገኙት ዕቃዎች በሙሉ ከንጹሕ ወርቅ እንጂ ከብር አልተሠሩም፤ ሰሎሞን ከኪራም መርከቦች ጋር በውቅያኖስ ላይ የሚጓዙ ሌሎች የተርሴስ መርከቦችም ነበሩት፤ እነርሱም በየሦስት ዓመት ወርቅን፥ ብርን፥ የዝሆን ጥርስን፥ ጦጣዎችንና ዝንጀሮዎችን ያመጡለት ነበር። ንጉሥ ሰሎሞን ከምድር ነገሥታት ሁሉ የሚበልጥ ሀብታምና ጥበበኛ ነበር። በመላው ዓለም የሚገኙ ሰዎችም ሁሉ እግዚአብሔር የሰጠውን ጥበብ የሞላበትን ንግግር ይሰሙ ዘንድ ወደ እርሱ መምጣት ይፈልጉ ነበር። ወደ እርሱም የሚመጡት ሁሉ የብርና የወርቅ፥ የልብስ፥ የጦር መሣሪያዎች፥ የሽቶ፥ የፈረሶችና የበቅሎዎች ስጦታዎችን ያመጡለት ነበር፤ ይህም በየዓመቱ የሚደረግ ነበር። ሰሎሞንም ሠረገሎችንና ፈረሶችን ሰበሰበ፤ እርሱም አንድ ሺህ አራት መቶ ሠረገሎችና ዐሥራ ሁለት ሺህ ፈረሰኞች ነበሩት፤ ከእነርሱም ከፊሉ ከእርሱ ጋር በኢየሩሳሌም፥ ሌሎቹ ደግሞ በልዩ ልዩ ከተሞች ተመድበው እንዲኖሩ አደረገ። በግዛቱም ዘመን ሁሉ በኢየሩሳሌም ብር እንደ ድንጋይ፥ የሊባኖስ ዛፍ ብዛት በይሁዳ ኰረብቶች ግርጌ በየትኛውም ስፍራ እንደሚበቅለው ሾላ ይቆጠር ነበር። ሰሎሞን ፈረሶችን ከግብጽና ከቀዌ ያስመጣ ነበር፤ የንጉሡም ነጋዴዎች ፈረሶችን በገንዘብ ገዝተው ከቀዌ ያመጡለት ነበር። ሠረገሎችን ከግብጽ አገር በማስመጣት፥ ለእያንዳንዱ ሠረገላ ስድስት መቶ ጥሬ ብር፥ ለእያንዳንዱም ፈረስ አንድ መቶ ኀምሳ ጥሬ ብር ይከፍሉ ነበር፤ ከዚያም እነርሱ ለሒታውያንና ለሶርያ ነገሥታት ይሸጡላቸው ነበር።
1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 10 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 10:14-29
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች