1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 14:21-40

1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 14:21-40 መቅካእኤ

“ቋንቋቸው እንግዳ በሆነ ሰዎች፥ በባዕዳንም አንደበት ለዚህ ሕዝብ እናገራለሁ፤ ይህም ሆኖ አይሰሙኝም፥ ይላል ጌታ” ተብሎ በኦሪትም ተጽፎአል። በዚህ ዓይነት፥ በልሳን መናገር ለማያምኑ የሚሆን ምልክት እንጂ ለሚያምኑት አይደለም፤ ትንቢት ግን ለሚያምኑ እንጂ ለማያምኑ አይደለም። እንግዲህ የቤተ ክርስቲያን ምእመናን በአንድነት በተሰበሰቡበት፥ ሁሉም በልሳን በመናገር ላይ እያሉ፥ እንግዶች ወይም የማያምኑ ሰዎች ወደ ጉባኤው ቢገቡ፥ አብደዋል አይሉምን? ነገር ግን ሁሉም ትንቢት በመናገር ላይ እያሉ፥ እንግዳ ወይም የማያምን ሰው ቢገባ፥ በሚሰማው ቃል ሁሉ ይወቀሳል፤ በሚሰማው ቃል ሁሉ ይመረመራል፤ በልቡም የተሰወረው ነገር ይገለጣል፤ እንዲሁም፥ “እግዚአብሔር በእርግጥ በመካከላችሁ ነው” በማለት በግንባሩ ተደፍቶ ለእግዚአብሔር ይሰግዳል። ወንድሞች ሆይ፤ እንግዲህ ምን እንበል? በምትሰበሰቡበት ጊዜ እያንዳንዱ መዝሙር አለው፤ ትምህርት አለው፤ መግለጥ አለው፤ በልሳን መናገር አለው፤ መተርጐም አለው። ይህ ሁሉ ግን ለማነጽ ይሁን። በልሳን የሚናገር ቢኖር፥ ሁለት ወይም ቢበዛ ሦስት በየተራ ይናገሩ፤ አንዱ ደግሞ ይተርጉም፤ የሚተረጉም ሰው ከሌለ ግን፥ በጉባኤ መካከል ዝም ይበልና ለራሱና ለእግዚአብሔር ይናገር። ሁለት ወይም ሦስት ነቢያት ይናገሩ፤ ሌሎቹ ደግሞ የተነገረውን በጥንቃቄ ያመዛዝኑ። ከተቀመጡትም መካከል አንድ ሰው አንድ ነገር ቢገለጥለት፥ የመጀመሪያው ተናጋሪ ዝም ይበል። እያንዳንዳችሁ እንድትማሩና እያንዳንዳችሁ እንድትበረታቱ፥ ሁላችሁ በየተራ ትንቢት መናገር ትችላላችሁ። የነቢያት መናፍስት ለነቢያት ይታዘዛሉ፤ እግዚአብሔር የሰላም አምላክ እንጂ፥ የሁከት አምላክ አይደለም። በቅዱሳን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዲሁ ነው። ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ዝም ይበሉ፤ ሕግም እንደሚለው እንዲታዘዙ እንጂ እንዲናገሩ አልተፈቀደላቸውም፤ ሴቶች ለማወቅ የሚፈልጉት አንዳንድ ነገር ካለ፥ ባሎቻቸውን በቤት ይጠይቁ፤ ምክንያቱም ሴት በቤተ ክርስቲያን መካከል ብትናገር የሚያሳፍር ነው። የእግዚአብሔር ቃል የወጣው ከእናንተ ነውን? ወይስ የደረሰው ወደ እናንተ ብቻ ነውን? ማንም ነቢይ ነኝ የሚል ወይም መንፈሳዊ ሰው ነኝ የሚል ቢኖር፥ ይህ የጻፍሁላችሁ የጌታ ትእዛዝ መሆኑን ይወቅ፤ ይህን አላውቅም የሚል ቢኖር እርሱም አይታወቅ። ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፤ ትንቢት ለመናገር በብርቱ ፈልጉ፤ በልሳን መናገርንም አትከልክሉ፤ ነገር ግን ሁሉም በአግባብና በሥርዓት ይሁን።