ስለዚህ ወዳጆቼ ሆይ! ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ። ልባሞች እንደ መሆናችሁ እላለሁ፤ የምለውን ነገር እናንተ ፍረዱ። የምንባርከው የበረከት ጽዋ፥ የክርስቶስን ደም መካፈል አይደለምን? የምንቆርሰውስ ኀብስት፥ የክርስቶስን ሥጋ መካፈል አይደለምን? አንድ ኀብስት ስለ ሆነ፥ ሁላችን ያን አንዱን ኀብስት እንካፈላለንና፥ እኛ ብዙዎች ብንሆንም አንድ አካል ነን። በሥጋ የሆነውን እስራኤልን ተመልከቱ፤ መሥዋዕቱን የሚበሉ የመሠዊያው ማኅበረተኞች አይደሉምን? እንግዲህ ምን እላለሁ? ለጣዖት የተሠዋ የሚረባ ነገር ነው? ወይስ ጣዖት የሚረባ ነገር ነው? አይደለም፤ ነገር ግን አሕዛብ የሚሠዉት ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለአጋንንት፤ ከአጋንንት ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ አልፈልግም። የጌታን ጽዋና የአጋንንትን ጽዋ ልትጠጡ አትችሉም፤ ከጌታ ማዕድና ከአጋንንት ማዕድ ልትካፈሉ አትችሉም። ወይስ ጌታን እናስቀናውን? እኛስ ከእርሱ ይልቅ እንበረታለንን? ሁሉ ነገር ተፈቅዶአል፤ ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም፤ ሁሉ ተፈቅዶአል፤ ነገር ግን ሁሉ የሚያንጽ አይደለም። እያንዳንዱ የሌሎችንም ጥቅም ያስብ እንጂ የራሱን ጥቅም አይፈልግ። ከሕሊና የተነሣ ሳትጠራጠሩ በሥጋ ገበያ የሚሸጠውን ሁሉ ብሉ፤ ምድር የጌታ ነውና፥ በእርሷ የሞላባት ሁሉ። ከማያምኑ ሰዎች አንዱ ቢጠራችሁ እናንተም ለመሄድ ብትፈልጉ ከሕሊና የተነሣ ሳትጠራጠሩ የሚያቀርቡላችሁን ሁሉ ብሉ። ማንም ግን “ይህ ለጣዖት የተሠዋ ነው፤” ቢላችሁ ይህን በነገራችሁ ሰው ምክንያትና በኅሊናም ምክንያት ሥጋውን አትብሉ፤ ስለ ሌላው ሰው ሕሊና ማለቴ እንጂ ስለ ራሳችሁ ሕሊና አይደለም። ነጻነቴ በሌላ ሰው ሕሊና የሚፈርድ ኧረ ለምንድን ነው? እኔም በምስጋና ብበላ፥ በነገሩ ስለማመሰግንበት ስለምን እሰደባለሁ? እንግዲህ ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ ወይም ማናቸውንም ነገር ስታደርጉ፥ ሁሉን ነገር ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት። ለአይሁድም ይሁን ለግሪክም እንዲሁም ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ማሰናከያ አትሁኑ። እኔ ደግሞ የራሴን ጥቅም ሳልፈልግ ነገር ግን ብዙዎቹ እንዲጠቀሙ፥ በሁሉ ነገር ሰውን ሁሉ ደስ ለማሰኘት የምጥረው፥ ይድኑ ዘንድ ነው።
1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10 ያንብቡ
ያዳምጡ 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10:14-33
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች