1ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 27

27
የሠራዊቱ አከፋፈል
1የእስራኤልም ልጆች የአባቶች ቤቶች አለቆች የሺህ አለቆች የመቶ አለቆችም በክፍሎች ምደባ ሁሉ ንጉሡን ያገለገሉት ሹማምንት እንደ ቁጥራቸው እነዚህ ነበሩ። እነዚህም ክፍሎች እያንዳንዳቸው ሀያ አራት ሺህ ሆነው በዓመት ውስጥ ባሉት ወራት ሁሉ በየወሩ ይገቡና ይወጡ ነበር። 2ለመጀመሪያው ወር የዘብድኤል ልጅ ያሾብዓም በአንደኛው ክፍል ላይ ተሹሞ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ። 3እርሱ ከፋሬስ ልጆች ነበረ፤ ለመጀመሪያ ወር በሠራዊቱ አለቆች ሁሉ ላይ ተሾሞ ነበር። 4በሁለተኛውም ወር ባለው ክፍል ላይ አሆሃዊው ዱዲ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ። 5ለሦስተኛው ወር ሦስተኛው የሠራዊቱ አለቃ የካህኑ የዮዳሄ ልጅ በናያስ ነበረ፤ በእነርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ። 6ይህ በናያስ በሠላሳው መካከል ኃያል ሆኖ ሠላሳውን ያዝ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ልጁ ዓሚዛባድ ተሹሞ ነበር። 7ለአራተኛው ወር አራተኛው አለቃ የኢዮአብ ወንድም አሣሄል፥ ከእርሱም በኋላ ልጁ ዝባድያ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ። 8ለአምስተኛው ወር አምስተኛው አለቃ ይዝራዊው ሸምሁት ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባለላት ነበሩ። 9ለስድስተኛው ወር ስድስተኛው አለቃ የቴቁሐዊው የዒስካ ልጅ ዒራስ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ። 10ለሰባተኛው ወር ሰባተኛው አለቃ ከኤፍሬም ልጆች የሆነ ፍሎናዊው ሴሌስ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ። 11ለስምንተኛው ወር ስምንተኛው አለቃ ከዛራውያን የነበረው ኩሳታዊው ሲቦካይ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ። 12ለዘጠነኛው ወር የዘጠነኛው አለቃ ከብንያማውያን የነበረው ዓናቶናዊው አቢዔዘር ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ። 13ለአሥረኛው ወር አሥረኛው አለቃ ከዛራውያን የነበረው ነጦፋዊው ኖኤሬ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ። 14ለዐሥራ አንደኛው ወር ዐሥራ አንደኛው አለቃ ከኤፍሬም ልጆች የነበረው ጲርዓቶናዊው በናያስ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ። 15ለዐሥራ ሁለተኛው ወር ዐሥራ ሁለተኛው አለቃ ከጎቶንያል ወገን የነበረው ነጦፋዊው ሔልዳይ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ።
የነገዶች አለቆች
16በእስራኤልም ነገዶች ላይ እነዚህ ነበሩ በሮቤላውያን ላይ የዝክሪ ልጅ አልዓዛር አለቃ ነበረ፤ በስማዖናውያን ላይ የመዓካ ልጅ ሰፋጥያስ አለቃ ነበረ፤ 17በሌዊ ላይ የቀሙኤል ልጅ ሐሸብያ አለቃ ነበረ፤ በአሮን ላይ ሳዶቅ አለቃ ነበረ፤ 18በይሁዳ ላይ ከዳዊት ወንድሞች ኢሊሁ አለቃ ነበር፤ በይሳኮር ላይ የሚካኤል ልጅ ዖምሪ አለቃ ነበረ፤ 19በዛብሎን ላይ የአብድዩ ልጅ ይሽማያ አለቃ ነበረ፤ በንፍታሌም ላይ የዓዝሪኤል ልጅ ኢያሪሙት አለቃ ነበረ፤ 20በኤፍሬም ልጆች ላይ የዓዛዝያ ልጅ ሆሴዕ አለቃ ነበረ፤ በምናሴ ነገድ እኩሌታ ላይ የፈዳያ ልጅ ኢዩኤል አለቃ ነበረ፤ 21በገለዓድ ባለው በምናሴ ነገድ እኩሌታ ላይ የዘካርያስ ልጅ አዶ አለቃ ነበረ፤ በብንያም ላይ የአብኔር ልጅ የዕሢኤል አለቃ ነበረ፤ 22በዳን ላይ የይሮሐም ልጅ ዓዛርኤል አለቃ ነበረ፤ እነዚህ የእስራኤል ነገዶች አለቆች ነበሩ። 23#ዘፍ. 15፥5፤ 22፥17፤ 26፥4።ጌታ ግን እስራኤልን እንደ ሰማይ ከዋክብት ለማብዛት ተናግሮ ነበርና ዳዊት ከሀያ ዓመት በታች የነበሩትን አልቈጠረም። 24#2ሳሙ. 24፥15፤ 1ዜ.መ. 21፥1-14።የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ መቁጠር ጀመረ፥ ነገር ግን አልፈጸመም፤ ስለዚህም በእስራኤል ላይ ቁጣ ወረደ፥ ቁጥራቸውም በንጉሡ በዳዊት መዝገብ አልተጻፈም።
ሌሎች ሹማምንት
25በንጉሡም ቤተ መዛግብት ላይ የዓዲኤል ልጅ ዓዛሞት ሹም ነበረ፤ በአገሩም በከተሞቹም በመንደሮቹም በግንቦቹም ባሉ ቤተ መዛግብት ላይ የዖዝያ ልጅ ዮናታን ሹም ነበረ፤ 26መሬቱን በሚያበጃጁትና እርሻውን በሚያርሱት ላይ የክሉብ ልጅ ዔዝሪ ሹም ነበረ፤ 27በወይንም ቦታዎች ላይ ራማታዊው ሰሜኢ ሹም ነበረ፤ ለወይንም ጠጅ ዕቃ ቤት በሚቀርበው በወይኑ ምርት ላይ ሸፋማዊው ዘቢድ ሹም ነበረ። 28በቈላውም ውስጥ ባሉት በወይራውና በሾላው ዛፎች ላይ ጌድራዊው በአልሐናን ሹም ነበረ፤ በዘይቱም ቤቶች ላይ ኢዮአስ ሹም ነበረ፤ 29በሳሮንም በሚሰማሩ ከብቶች ላይ ሳሮናዊው ሰጥራይ ሹም ነበረ፤ በሸለቆቹም ውስጥ በነበሩት ከብቶች ላይ የዓድላይ ልጅ ሻፋጥ ሹም ነበረ፤ 30በግመሎችም ላይ እስማኤላዊው ኡቢያስ ሹም ነበረ፤ በአህዮቹም ላይ ሜሮኖታዊው ዬሕድያ ሹም ነበረ፤ በመንጎቹም ላይ አጋራዊው ያዚዝ ሹም ነበረ። 31እነዚህ ሁሉ በንጉሡ በዳዊት ሀብት ላይ ሹሞች ነበሩ።
32አስተዋይና ጸሐፊ የነበረው የዳዊት አጎት ዮናታን አማካሪ ነበረ፤ የሐክሞኒም ልጅ ይሒኤል የንጉሡን ልጆች ያገለግል ነበረ፤ 33አኪጦፌልም የንጉሡ አማካሪ ነበረ፤ አርካዊውም ኩሲ የንጉሡ ወዳጅ ነበረ፤ 34ከአኪጦፌልም ቀጥሎ የበናያስ ልጅ ዮዳሄና አብያታር ነበሩ፤ ኢዮአብም የንጉሡ ሠራዊት አለቃ ነበረ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ