1ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 26

26
የደጁ ጠባቂዎች
1የደጁም ጠባቂዎች ምድባቸው እንደዚህ ነበር፤ ከቆሬያውያን ከአሳፍ ልጆች የቆሬ ልጅ ሜሱላም። 2ሜሱላም ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም በኩሩ ዘካርያስ፥ ሁለተኛው ይዲኤል፥ ሦስተኛው ዮዛባት፥ አራተኛው የትኒኤል፥ 3አምስተኛው ኤላም፥ ስድስተኛው ይሆሐናን፥ ሰባተኛው ኤሊሆዔናይ ነበሩ። 4#2ሳሙ. 6፥11፤ 1ዜ.መ. 13፥14።ዖቤድ-ኤዶም ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም በኩሩ ሸማያ፥ ሁለተኛው ዮዛባት፥ ሦስተኛው ኢዮአስ፥ አራተኛው ሣካር፥ አምስተኛው ናትናኤል፥ 5ስድስተኛው ዓሚኤል፥ ሰባተኛው ይሳኮር፥ ስምንተኛው ፒላቲ ነበሩ፤ እንዲህም የሆነለት እግዚአብሔር ስለ ባረከው ነበር። 6ለልጁም ለሸማያ ደግሞ ልጆች ተወለዱለት፤ ጽኑዓንም ኃያላን ነበሩና በአባታቸው ቤት ሠለጠኑ። 7የሸማያ ልጆች፤ ዖትኒ፥ ራፋኤል፥ ዖቤድ፥ ኤልዛባድ ነበሩ፤ ኤልዛባድም ኃያላን ወንድሞች የነበሩት እነርሱም ኤሊሁና ሰማክያ ነበሩ። እነዚህ ሁሉ የዖቤድ-ኤዶም ልጆች ነበሩ፤ 8እነርሱም ልጆቻቸውም ወንድሞቻቸውም ለማገልገል ኃያላን የነበሩ የዖቤድ-ኤዶም ልጆች ስልሳ ሁለት ነበሩ። 9ለሜሱላም ኃያላን የነበሩ ዐሥራ ስምንት ልጆችና ወንድሞች ነበሩት። 10ከሜራሪም ልጆች ለነበረው ለሖሳ ልጆች ነበሩት፤ አለቃውም ሽምሪ ነበረ፤ በኩር አልነበረም፥ አባቱ ግን አለቃ አደረገው፤ 11ሁለተኛውም ኬልቅያስ፥ ሦስተኛው ጥበልያ፥ አራተኛው ዘካርያስ ነበሩ፤ የሖሳ ልጆችና ወንድሞች ሁሉ ዐሥራ ሦስት ነበሩ።
12እንደ ወንድሞቻቸው ሆነው በጌታ ቤት እንዲያገለግሉ በየአለቆቻቸው የደጁ ጠባቂዎች ሰሞነኞች እነዚህ ነበሩ። 13በበሩም ሁሉ ለማገልገል በየአባቶቻቸው ቤቶች ታናሹና ታላቁ በተመሳሳይ መልኩ ይዕጣ ተጣጣሉ። 14ለሰሌምያም በምሥራቅም በኩል ዕጣ ወጣለት። ለልጁም ብልህ አማካሪ ለሆነው ለዘካርያስ ዕጣ ጣሉ፤ የእርሱም ዕጣ በሰሜን በኩል ወጣ። 15ለዖቤድ-ኤዶም ዕጣው በደቡብ በኩል ወጣ፥ ለልጆቹም የዕቃ ግምጃ ቤቱን እንዲጠብቁ ዕጣ ወጣላቸው። 16ለሰፊንና ለሖሳ በዐቀበቱም መንገድ ባለው በሸሌኬት በር በምዕራብ በኩል ዕጣ ወጣላቸው፤ ይህም ጥበቃ ከጥበቃ ትይዩ ነበር። 17በምሥራቅ በኩል ስድስት ሌዋውያን ነበሩ፤ በሰሜን በኩል ለየዕለቱ አራት፥ በደቡብ በኩል ለየዕለቱ አራት፥ ለዕቃ ቤቱም ሁለት ሁለት ነበሩ። 18በምዕራብ በኩል በምሶሶው አጠገብ ባለው መንገድ አራት፥ በምሶሶም አጠገብ ሁለት ነበሩ። 19ከቆሬና ከሜራሪ ልጆች የነበሩ የደጁ ጠባቂዎች ሰሞን ይህ ነበረ።
የቤተ መዛግብት ሹማምንት የጦር አዛዦችና ፈራጆች
20ከሌዋውያን አኪያ በእግዚአብሔር ቤት በሚሆኑ ቤተ መዛግብትና በንዋየ ቅዱሳቱ ቤተ መዛግብት ላይ ተሾሞ ነበር። 21የለአዳን ልጆች፤ የለአዳን ቤተሰብ የሆኑ የጌድሶናውያን ልጆች፥ ለጌድሶናዊው ከለአዳን ቤተሰብ የሆኑ የአባቶች ቤቶች አለቆች ይሒኤሊ ነበር፤ 22የይሒኤሊ ልጆች፤ በጌታ ቤት በቤተ መዛግብት ላይ ተሹመው የነበሩት ዜቶም፥ ወንድሙም ኢዮኤል ነበሩ። 23ከእንበረማውያን፥ ከይስዓራውያን፥ ከኬብሮናውያን፥ ከዑዝኤላውያን፤ 24የሙሴ ልጅ የጌርሳም ልጅ ሱባኤል በቤተ መዛግብት ላይ ተሹሞ ነበር። 25ወንድሞቹም፤ ለአልዓዛር ልጁ ረዓብያ፥ ልጁም የሻያ፥ ልጁም ኢዮራም፥ ልጁም ዝክሪ፥ ልጁም ሰሎሚት ነበሩ። 26ይህ ሰሎሚትና ወንድሞቹ ንጉሡ ዳዊትና የአባቶች ቤቶች አለቆች፥ ሻለቆችና የመቶ አለቆች የሠራዊቱም አዛዦች፥ በቀደሱት በንዋየ ቅድሳቱ ቤተ መዛግብት ሁሉ ላይ ተሾመው ነበር። 27በጦርነትም ከተገኘው ምርኮ የጌታን ቤት ለመሥራት ስጦታ ቀድሰው ሰጡ። 28ባለ ራእዩም ሳሙኤል፥ የቂስም ልጅ ሳኦል፥ የኔርም ልጅ አበኔር፥ የጽሩያም ልጅ ኢዮአብ የቀደሱት ንዋየ ቅድሳት ሁሉ ከሰሎሚትና ከወንድሞቹ ሥልጣን በታች ነበረ።
29ከይስዓራውያን ከናንያና ልጆቹ ሹማምትና ፈራጆች እንዲሆኑ በውጭው በሚከናወነው ሥራ በእስራኤል ላይ ተሾመው ነበር። 30ከኬብሮናውያን ሐሸብያና ወንድሞቹ፥ ጽኑዓን የነበሩት ሺህ ሰባት መቶ ሰዎች፥ ለጌታ ሥራ ሁሉ ለንጉሡም አገልግሎት በዮርዳኖስ ማዶ በምዕራብ በኩል ባለው በእስራኤል ላይ ተሾመው ነበር። 31ከኬብሮናውያንም እንደ አባቶች ቤቶች ትውልዶች የኬብሮናውያን አለቃ ይሪያ ነበረ። ዳዊት በነገሠ በአርባኛው ዓመት ይፈልጉአቸው ነበር፤ በእነርሱም መካከል በገለዓድ ኢያዜር ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ተገኙ፤ 32ወንድሞቹም ጽኑዓን የነበሩት የአባቶች ቤቶች አለቆች ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ። ንጉሡም ዳዊት ለእግዚአብሔር ጉዳይ ሁሉና ለንጉሡ ጉዳይ በሮቤላውያንና በጋዳውያን በምናሴም ነገድ እኩሌታ ላይ ሹሞች አደረጋቸው።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ