ትንቢተ ዘካርያስ 8:14-23

ትንቢተ ዘካርያስ 8:14-23 አማ05

“እኔ የሠራዊት አምላክ ይህን ተናግሬአለሁ፤ የቀድሞ አባቶቻችሁ ባስቈጡኝ ጊዜ ባለመራራት ቅጣት ላመጣባችሁ ወሰንኩ። ለኢየሩሳሌምና ለይሁዳ ሕዝብ መልካምን ነገር ማድረግ ወስኜአለሁና አይዞአችሁ፤ አትፍሩ። እናንተ ልታደርጉት የሚገባ ነገር ይህ ነው፦ እርስ በርሳችሁ እውነትን ተነጋገሩ፤ በፍርድ ሸንጎዎቻችሁ ሰላም የሚገኝበትን እውነተኛ ፍርድ ስጡ። እርስ በርሳችሁ ለመጐዳዳት አንዱ በሌላው ላይ ተንኰል አያስብ፤ በሐሰት አትማሉ፤ እኔ ይህን ሁሉ እጠላለሁ” ይላል እግዚአብሔር። የሠራዊት አምላክ እንዲህ አለኝ፦ “በአራተኛው፥ በአምስተኛው፥ በሰባተኛውና በዐሥረኛው ወር ትጠብቁት የነበረው ጾም ሁሉ ለይሁዳ ሕዝብ የተድላና የደስታ በዓል ይሆንላቸዋል፤ እናንተ ግን እውነትንና ሰላምን ውደዱ።” የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል፦ “ሌሎች ሕዝቦችና በብዙ ከተሞች የሚኖሩ ሰዎች ወደ ኢየሩሳሌም የሚጐርፉበት ጊዜ ይመጣል። የአንድ ከተማ ነዋሪዎች ወደ ሌላ ከተማ ሄደው ‘ኑ! ከሠራዊት አምላክ ቸርነትን እንለምን፤ እኛም ወደዚያ መሄዳችን ነው!’ ይሉአቸዋል። በዚህ ዐይነት ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር ለመስገድና የእርሱንም በረከት ያገኙ ዘንድ ለመጸለይ ብዙ ሰዎችና ታላላቅ ሕዝቦች ወደ ኢየሩሳሌም ይመጣሉ። በእነዚያ ቀኖች ዐሥር የሌላ አገር ሰዎች ወደ አንድ አይሁዳዊ ቀርበው የልብሱን ዘርፍ በመያዝ ‘እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር መሆኑን ስለ ሰማን ከእናንተ ጋር እንሂድ’ ይሉታል።”