አማትዋ ናዖሚ ሩትን እንዲህ አለቻት፦ “ልጄ ሆይ! መልካም ይሆንልሽ ዘንድ የተመቻቸ ኑሮ የምትኖሪበትን ሁናቴ ልፈልግልሽ ይገባል። ስትቃርሚ አብረውሽ የነበሩት ሴቶች የሚያገለግሉት ቦዔዝ የቅርብ ዘመዳችን ነው፤ እነሆ! እርሱ ዛሬ ማታ ገብስ ይወቃል፤ ስለዚህ ሰውነትሽን ታጠቢና ሽቶ ተቀቢ፤ የክት ልብስሽንም ልበሺ፤ ከዚህ በኋላ እርሱ ገብሱን ወደሚወቃበት አውድማ ሂጂ፤ ነገር ግን እስከሚበላና እስከሚጠጣ ድረስ በፊቱ አትታዪ። የት እንደሚተኛ ካረጋገጥሽ በኋላ፥ እንቅልፍ ሲወስደው ወደ እርሱ ቀረብ በዪና ከግርጌው በኩል ልብሱን ገልጠሽ በእግሩ አጠገብ ተኚ፤ ምን ማድረግ እንደሚገባሽ እርሱ ራሱ ይነግርሻል።” ሩትም “ያልሽውን ሁሉ አደርጋለሁ” አለቻት። ስለዚህ ሩት ወደ አውድማው ሄዳ ልክ ዐማትዋ እንደ ነገረቻት አደረገች። ቦዔዝ ከበላና ከጠጣ በኋላ ደስ ብሎት ነበር፤ ወደ ገብሱም ክምር ሄዶ ጋደም አለና አንቀላፋ፤ ሩትም በቀስታ ወደ እርሱ ተጠጋች፤ ልብሱንም ገለጥ አድርጋ በእግሩ አጠገብ ተኛች። ወደ እኩለ ሌሊት ገደማም ቦዔዝ ድንገት ነቅቶ ሲገላበጥ አንዲት ሴት በግርጌ ተኝታ በማግኘቱ ተደነቀ፤ “አንቺ ማን ነሽ?” ብሎም ጠየቃት። እርስዋም “ጌታዬ ሆይ! አገልጋይህ እኔ ሩት ነኝ፤ አንተ የቅርብ ዘመድ ስለ ሆንክ ለእኔ ኑሮ የማሰብ ኀላፊነት አለብህ፤ ስለዚህ ልብስህን ባገልጋይህ ላይ ጣል አለችው።” ቦዔዝም እንዲህ አላት፤ “ልጄ ሆይ! እግዚአብሔር ይባርክሽ፤ አሁን በምታደርጊው ነገር ከዚህ በፊት ለዐማትሽ ካደረግሽው የሚበልጥ ታማኝነት አሳይተሻል፤ ብትፈልጊ ኖሮ ወደ ሀብታም ወይም ወደ ድኻ ወጣት መሄድ ትችይ ነበር፤ ነገር ግን ይህን ማድረግ አልፈለግሽም፤ ልጄ ሆይ! አትፍሪ፤ ከእንግዲህ ወዲህ በከተማው ያሉ ሰዎች ሁሉ አንቺ መልካም ሴት መሆንሽን ያውቃሉ፤ የምትፈልጊውን ሁሉ አደርግልሻለሁ።
መጽሐፈ ሩት 3 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ሩት 3:1-11
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች